ኢሳት (ግንቦት 2 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ አለም አቀፍ ሃገራትና አበዳሪ አካላት የሚያገኘው የብድርና የእርዳታ ፍሰት እየቀነሰ መምጣቱ ጉዳዩን የሚከታተለው የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ረቡዕ አስታወቀ።
በተለይ ያደጉ አገሮች በራሳቸው ችግር ምክንያት ሲያደርጉ የቆዩትን የፋይናንስ ድጋፍ እያቋረጡ መሆኑን የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አዳም ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል።
የብድርና የእርዳታ ፍሰቱ መቀነስ ከአጠቃላይ ወጪ አንጻር ተጽዕኖ ይኖረዋል ያሉት ሃላፊው በተለይ ከአደጉ አገሮች የሚገኘው ብድርና ዕርዳታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበረው አስረድተዋል።
ባለፈው አመት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለታዳጊ ሃገራት በሚሰጠው አለም አቀፍ የልማት ድጋፍ ላይ ያደረገው የገንዘብ ቅነሳ ኢትዮጵያን ተጎጂ ማድረጉ ተገልጿል።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በወሰደው በዚሁ የድጎማ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍን ያጣች ሲሆን፣ ታንዛኒያ፣ ዩንጋንዳ፣ ማላዊና ኬንያም መጠነኛ ቅነሳ ተደርጎባቸዋል።
ከአለም አቀፍ አካላት ዘንድ በሚገኝ የገንዘብ ልገሳ በጀታቸውን የሚደጉሙ ሃገራት አሜሪካ በወሰደችው ዕርምጃ የፋይናንስ ጫና ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ሃገሪቱ ያጋጠማትን የብድርና የድጋፍ መቀነስ ለመቅርፍ፣ የውጭ ንግድና ኢንቨሰትመንት ማስፋፋት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ሃላፊው አክለው አስታውቀዋል።
ይሁንና ካለፉት ሶስትና አራት አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ እየቀነሰ መምጣቱ ችግሩን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ላይ ስጋት ማሳደሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በተያዘው በጀት አመት ባለፉት ሰባት ወራት ከውጭ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም ሊገኝ የቻለው ግን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ታውቋል።
በ2008 አም በአጠቃላይ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታስቦ 2.9 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ ከውጭ ንግድ መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመስራት ካቀዳቸው በርካታ የልማት ፕሮጄክቶች ከተለያዩ አካላት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍና ብድር ለማግኘት ፍላጎት እንደነበረው ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና ከተለያዩ ለጋሽ ሃገራት የሚገኘው ብድርና ድጋፍ እየቀነሰ መምጣት በልማት እቅዱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተሰግቷል።
የኢትዮጵያ የብድር ዕዳ እየጨመረ መምጣቱ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገቱና በዋጋ ግሽበት ላይ የራሱን አስተዋጽዖ እያሳደረ እንደሚገኝ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ 2015 መጨረሻ ድረስ የሃገሪቱ አጠቃላይ የብድር መጠን 36 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment