ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2009)
በቅርቡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል በድንበር ዙሪያ ቁጥጥርን ለማጠናከር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ሰራዊቶች በአዋሳኝ ድንበር ዙሪያ መስፈራቸውን የሱዳን ባለስልጣናት ረቡዕ አስታወቁ።
የሁለቱ ሃገራት ተወካዮች ባለፈው ወር በባህር ዳር ከተማ ባካሄዱት የድንበር ውይይት በአካባቢው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የአደንዛዥ ዕፅን ይቆጣጠራል የተባለ የጋራ ሰራዊት እንዲሰፍር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
የዚህኑ የመግባቢያ ሰነድ መፈረም ተከትሎ የኢትዮጵያና የሱዳን ወታደሮች ከካርቱም ከተማ በ300 ማይል ርቀት ላይ በሚገኝ የድንበር ዙሪያ ቁጥጥር ማድረግ መጀመራቸውን ሱዳን ትሪብዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
የሱዳን የሰናር ግዛት የድንበር መምሪያ ሃላፊ የሆኑት ፋይድ አል-ዋዉላ-ሞሃመድ በድንብር ዙሪያ የሰፈሩት የሁለቱ ሃገራት ሰራዊቶች በአካባቢው ድንበር የመጣስ ድርጊትን የመቆጣጠር ሃላፊነት ያለው እንደሆነ ለጋዜጣው አስረድተዋል። በሁለቱ ሃገራት የድንበር አዋሳኝ ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድንበሩ የማካለል ውሳኔ ተካሄዶበታል እየተባሉ በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ከገዳሬፍ አካባቢ እንዲለቁ መገደዳቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ የሱዳን ባለስልጣናት በዚሁ የድንበር አካባቢ የሚነሱ የይገባኛል ጥያቄን እልባት ለመስጠት ድንበሩ እንዲካለል ከአንድ አመት በፊት በካርቱም ስምምነት ማደረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና ድንበሩን የማካለሉ ስምምነት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በድንበር አካባቢ የሰፈሩት የሁለቱ ሃገራት ወታደሮች በዋነኛነት ድንበርን የሚያቋርጡ ሰዎችን የመቆጣጠር ስልጣን እንደተጣለባቸው የሱዳን ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ይሁንና በድንበር አካባቢ ቁጥጥርን እያደረጉ ስላሉት የሁለቱ ሃገራት ወታደሮች ቁጥር የሱዳንም ሆነ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
ኢትዮጵያና ሱዳን ባለፈው ወር ባካሄዱት ተመሳሳይ ስምምነት አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ሃገር ተቃዋሚ ወይም አማጺ ቡድን እንደማይደግፍ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውም የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ ከሱዳን በምትዋሰንበት የድንበር ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በታጠቁ ሃይሎች ጥቃት ሲፈጸም መቆየቱን ስትገልፅ የቆየች ሲሆን በቅርቡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በተሽከርካሪ ላይ ጥቃት በማድረስ ከ10 በላይ ሰዎች መግደላቸውም አይዘነጋም።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከሱዳን በመሻገር በአባይ ግድብ ላይ ጥቃትን ለማድረስ ሙከራን ሲያደርጉ ነበሩ የተባሉ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል የፌዴራል ፖሊስ ባለፈው ወር ይፋ አደርጓል።
No comments:
Post a Comment