ኢሳት (ግንቦት 23 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀጣዩ ሰኔ ወር ጀምሮ የሚቀርብላቸው የምግብ ድጋፍ አቅርቦት ሊያልቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለእርዳታ ጥሪው የሰጠው ምላሽ አነስተኛ መሆን የእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ድርጅቱ የድርቁን ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው አዲስ ሪፖርት ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መንግስት ባለፈው ወር ባወጡት አዲስ የተረጂዎች ቁጥር 5.6 ሚሊዮን የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 7.7 ሚሊዮን መድረሱ የሚታወስ ነው።
ይሁንና ድርቁን ለመከላከል እና ለተረጂዎች ድጋፍ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማምጣቱ ችግሩ እየተባባሰ ሊሄድ መቻሉ ታውቋል። የምግብ አቅርቦቱ እየተጠናቀቀ መምጣት 7.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ተረጂዎች ከሰኔ ወር ጀምሮ የምግብ አቅርቦት ላይኖር እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መንግስት የድርቁን አደጋ ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ከወራት በፊት ቢገልጹም እየተገኘ ያለው ድጋፍ ግን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ችግሩን ለመቅረፍ የምግብ አቅርቦት ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት በትንሹ ሶስት ወራትን የሚፈጅ ሲሆን፣ በቀጣዩ ወር ሊያልቅ ይችላል የተባለው የምግብ ክምችት በእርዳታ ተቋማት ዘንድ ስጋትን አሳድሯል። የአለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመመካከር ምግብን ከገበያ ማግኘት ለሚችሉ ተረጂዎች ጥሬ ገንዘብ ለመስጠት አማራጭ መያዙም ታውቋል።
በሶማሌ ክልል ያለው የምግብ አጥረት እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ያለው የምግብ ዕርዳታ ክምችት ወደ ማለቅ መሆኑ አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል ሲል የተባበሩት መንግስታት የእርዳት ማስተባበሪያ ቢሮ በሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።
የኦሮሚያ፣ አፋር ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች የተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑ ይገልጻል።
ከአንድ አመት በፊት ለ10 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ምክንያት የነበረው የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ በአራቱ ክልሎች መከሰቱ በዕርዳታ አቅርቦት ላይ ጫና ማሳደሩንም የዕርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ያለው የድርቅ አደጋ ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ከ700 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ይሁንና፣ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም።
No comments:
Post a Comment