ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2009)
የሶማሊያው አዲስ ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብዱላሂ ከኢትዮጵያ ጋር ተፈጥሯል በተባለው አለመተማመን ዙሪያ ለመምከር ረቡዕ በአዲስ አበባ ጉብኝት ማድረግ መጀመራቸውን ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል የሃገሪቱ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ ረቡዕ ዘገበ።
ፕሬዚደንት አብዱላሂ ኢትዮጵያን ከመጎብኘታቸው በፊት በአምስት ሃገራት ጉዞ ያደረጉ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊም እጅግ አስቸጋሪም ነው ሲሉ የአፍሪካ ቀንድ የታሪክ ምሁር የሆኑት ጀራልድ ፕሩኒየር ለራዲዮ ጣቢያው ገልጸዋል።
ፕሬዚደንቱ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለመምከር የወሰደባቸው ጊዜ ከዚህ በፊት የሶማሊያ ተመራጭ ፕሬዚደንቶች ሲያደርጉ ከቆየው ጋር ሲነጻጸር በጣም የዘገየ መሆኑንም ሚሰተር ጀራልድ አስረድተዋል።
ከሁለት ወር በፊት በሃገሪቱ የተካሄደን ምርጫ ለማሸነፍ የቻሉት ፕሬዚደንት አብደላሂ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሃገሪቱ እንዲወጡላቸው የተባለው አቋም ለድል እንዳበቃቸው ሲገልጹ ቆይቷል።
ይሁንና ፕሬዚደንቱ እስካሁን ድረስ በሃገራቸው ስላሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጉዳይ በይፋ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ጉዳዩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ወቅት መወያያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር አሰማርታ ካለው ወታደር በተጨማሪ ቁጥሩ ያልታወቅ ሰራዊትን በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች ለአመታት ማስፈሯ ይታወሳል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ያላት አቋም በሶማሊያ የተለያዩ ፖለቲከኞች ዘንድ የሃሳብ ልዩነት እንዳለውና ሁኔታው ከወራት በፊት ተካሄዶ በነበረው ምርጫ ወቅት መንጸባረቁን የሶማሊያ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በኢትዮጵያ የሁለት ቀን ቆይታ የሚኖራቸው የሶማሊያው ፕሬዚደንት ኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅነት ካላትና ራሷን ነጻ ሃገር አድርጋ ባወጀችው የሶማሊላንድ ጉዳይ ዙሪያም እንደሚመክሩ የፈረንሳይ ሬድዮ ጣቢያ ዘገባ አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ረቡዕ በአዲስ አበባ የገቡት ፕሬዚደንት አብዱላሂ በሃገራቸው የሰላም ሂደት ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ውይይትን እንደሚያካሄዱም ታውቋል።
No comments:
Post a Comment