ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)
አሜሪካ በቅርቡ ለአለም አቀፍ ድጋፍ በምትሰጠው የገንዘብ ድጎማ ላይ ያስተላለፈችው የበጀት ቅነሳ፣ ኢትዮጵያ ዋነኛ ተጎጂ ማድረጉ ተገለጸ። ለኢትዮጵያና ኡጋንዳ የሚሰጠው ድጋፍ እንደሚቀንስም ተመልክቷል።
ሃገሪቱ በተያዘው ሳምንት ባቀረበችው የ2017/2018 በጀት እቅድ በአለም አቀፍ የእርዳታ ላይ የ31 በመቶ አካባቢ ቅናሽ ማድረጓን ዘኢስት አፍሪካን የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
በዚሁ የአሜሪካ ዕርምጃ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ከአፍሪካ ዋነኛ ተጎጂ መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣዩ የአሜሪካ በጀት አቅድ የ132 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የድጋፍ ቅነሳ የሚደረግበት ሲሆን፣ ዩጋንዳ ወደ 68 ሚሊዮን ዶላር እንደምታጣ ለመረዳት ተችሏል።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለተለያዩ ሃገራት ሲሰጥ የቆየው የልማት ድጋፍ እንዲቀንስና ወደ ኢኮኖሚያዊ እገዛ እንዲለወጥ አቋም መያዛቸው ታውቋል። አዲሱ የአሜሪካ ፖሊሲ ለረጅም አመታት ቀጥተኛ የልማት ፖሊሲ ድጋፍ ሲቀበሉ የቆዩ ሃገራት ድጋፋቸው እጅጉኑ እንዲቀንስ ማድረጉን የሃገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያና ዩጋንዳ በተጨማሪ ሩዋንዳና ታንዛኒያ እያንዳንዳቸው የ51 እና የ12 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ቅነሳ የሚደረግባቸው ሲሆን፣ ሶማሊያ የ36 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጭማሪን በማግኘት ከአፍሪካ ብቸኛ ሃገር ሆናለች።
ኬንያ በ12 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ደቡብ ሱዳንና ቡሩንዲ ደግሞ እያንዳንዳቸው የ11 እና የ10 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የእርዳታ ቅነሳ እንደሚደረግባቸው ለመረዳት ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያ የ132 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በማጣት ከአፍሪካ ግንባት ቀደም ሃገር ሆና ተቀምጣለች።
አዲሱ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለልማት ድጋፍ ሲሰጥ የቆየውን የገንዘብ ዕርዳታ ወደ ኢኮኖሚያዊ ድጎማ በመቀየር ጥቅሟን በምታስጠበቅባቸው ሃገራት የኢኮኖሚና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲሰፍን እቅድ መያዟ ተመልክቷል።
በዚሁ የሃገሪቱ አዲስ የድጋፍ ስልት ለግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን ኢትዮጵያ ጨምሮ በርካታ ሃገራት ሲያገኙ የቆዩት የልማት ድጋፍ እንደሚቀር ተገልጿል።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ዩጋንዳ ሲያገኙ የነበረው የልማት ድጋፍ ወደ ኢኮኖሚያዊ ድጎማ ተቀይሮ እያንዳንዳቸው 200 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
ቡሩንዲ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ ምንም አይነት የልማት ድጋፍ ሳይቀበሉ የቆዩ ሃገራት ሲሆኑ በአሜሪካ አዲስ የድጎማ ፖሊሲ ልዩ ትኩረት እንደተሰጣቸው ለመረዳት ተችሏል።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ወር ሃገሪቱ በአለም ዙሪያ ስትሰጥ የቆየችው የቤተሰብ ዕቅድ ደግሞ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውም ይታወሳል። አሜሪካ ለልማት ድጋፍ ስትሰጠው የቆየችው ዕርዳታ እንዲቋረጥ ማድረጓ ድጋፉን ሲያገኙ በነበሩ ሃገራት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የተለያዩ አካላት ገልጸዋል።
የታንዛኒያው የፋይናንስ ሚኒስትር ፊሊፕ ምፓንጎ በአሜሪካ ዕርምጃ በበጀት እቅዱ ላይ ሃገራቸው እክል እንደሚያጋጥማት ለሃገራቸው መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ እስከአሁን ድረስ የሰጠችው ምላሽ የለም።
No comments:
Post a Comment