ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት የአለም ሃገራት ለመገናኛ ብዙሃን ነጻነት መከበር ቁርተኝነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ አሳሰቡ።
በየአመቱ ሚያዚያ 25 ፥ የሚከበረውን የአለም የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ቀንን አስመልክቶ መልዕክትን ያስተላለፉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የአለም ሃገራት መረጃዎችና ዜጎች በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ማዋከብና ማስፈራራት በአስቸኳይ ማቆም እንዳለባቸው ጥሪን አቅርበዋል።
የነጻ መገናኛ ብዙሃን ለሰላምና ፍትህ መጎልበት ወሳኝ ነው ያሉት ዋናው ጸሃፊው፣ ጋዜጠኞች ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ በመክተት ያልተሰሙ ድምፆች እንዲሰሙ የሚያደጉት ጥረት በመንግስታት ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የዘንድሮው የመገናኛ ብዙሃን ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ በኢንዶኔዢያ መዲና ጃካርታ ከተማ የተከበረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የአለም መሪዎች ለነጻ መገናኛ ብዙሃን ጥበቃ ማድረግ እንዳለባቸው ባስተላለፉት መልዕክት አክለው ገልጸዋል።
“በአለም ዙሪያ ያሉ ጋዜጠኞች ጥበቃን ካገኙ ቃላትና ፎቶዎቻቸው አለም የተሻለ የማድረግ ሃይል ይኖራቸዋል” ሲሉ አንቶኒ ጉተሬስ በቪዲዮ መልዕክታቸው ተናግረዋል።
አምነስቲ ኢንተርኛሽናል እንዲሁም በርካታ የሰብዓዊ መብት እና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለይ ጋዜጠኞች ላይ መዋከብን የሚፈጽሙ ሃገራት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪን አቅርበዋል።
የአለም የመገናኛ ብዙሃን ቀን ከሙያቸው ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ፣ እንዲሁም ግድያ የተፈጸመባቸውን ጋዜጠኞች በመዘከር በየአመቱ በልዩ ዝግጅት ይከበራል።
የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በሚያዚያ 23 ፥ 1993 የአለም የመገናኛ ብዙሃን ዕለት ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል።
የአለም ሃገራትን በአባልነት ያቀፈው ድርጅቱ ዕለቱን በማሰብ በየአመቱ አባል ሃገራቱ ለመገናኛ ብዙሃኑ መከበር ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ መልዕክቶችን እንደሚያቀርብበት የተባበሩት መንግስታት ራዲዮ ዘግቧል።
የድርጅት አባል ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 14 የሚጠጉ ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግ ከኢራን፣ ቱርክ፣ ሰሜን ኮሪያ ጋር ተርታ በመመደብ በአለም ካሉ ሃገራት መካከል ለጋዜጠኞች ከማይመቹ ሃገራት ተርታ ተመድባ ትገኛለች።
ባለፈው ሳምንት አመታዊ ሪፖርቱን ያወጣው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ኢትዮጵያ በአለም ያላት ደረጃ በማሽቆልቆል ከ142ኛ ወደ 150ኛ መውረዱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከአምስት አመት በፊት ተግባራዊ የተደረገው የጸረ-ሽብር ወንጀል ህግ በተለይ ጋዜጠኞችን ለማሰር ለመክሰስ እና ለማዋከብ እያገለገለ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment