ኢሳት (ግንቦት 16 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የተከሰተው የምግብ ዕጥረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊለወጥ እንደሚችል መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው የቅድመ ረሃብ ማስጠንቀቂያ ተቋም ረቡዕ አሳሰበ።
በአሁኑ ወቅት 7.7 ሚሊዮን የደረሰው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም አለም አቀፍ ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው አዲስ ሪፖርት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ 5.6 ሚሊዮን የነበረው የተረጂዎች ቁጥር 7.7 ሚሊዮን መድረሱን በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።
አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ያለው የድርቅ አደጋ ለሰዎች ህይወት ስጋት እየሆነ መምጣቱን ሲገልፁ ቆይተዋል።
በቅድመ ረሃብ ዙርያ ቅድመ ትንበያን የሚሰጠው አለም አቀፍ ድርጅት በተለይ በደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖሩ አርብተ አደሮች በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ክፉኛ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል አሳስቧል።
በእነዚሁ የሃገሪቱ በርካታ ስፍራዎች የምግብ እጥረቱ ለረሃብ አንድ ደረጃ ወደቀረው አራተኛ ደረጃ በመሸጋገር ላይ መሆኑን በምህጻረ ቃል ፊውስ ኔት (FEWS NET) የተሰኘው ድርጅት አመልቷል።
ባለፉት ሁለት ወራት በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች መጣል የነበረበት የበልግ ዝናብ በተገቢው መልኩ ባለመጣሉ ምክንያት ከሰኔ ወር ጀምሮ የምግብ እጥረቱ ወደ ከፋ ደረጃ መሸጋገር እንደሚጀምር ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ተመሳሳይ ሪፖርት የድርቅ አደጋ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለድርቁ ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ልገሳ በወቅቱ ባለመስጠቱ ምክንያት ድርቁ ሊባባስ መቻሉን የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።
አለም አቀፍ ተቋማት በሃገሪቱ አራት ክልሎች ውስጥ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ መልኩን ይቀይራል በማለት ቢያሳስቡም የመንግስት ባለስልጣናት ድርቁ በሰው ህይወት ላይ አደጋን እንዳያደርስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና፣ የሶማሌ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት የሞቱ ሲሆን የምግብ እጥረት ለአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ መቀስቀስ ምክንያት መሆኑ ተመልቷል።
የአለም ጤና ድርጅት በሶማሌ ክልል እየተስፋፋ ባለው በዚሁ የበሽታ ስርጭት ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ700 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሽታው እንዲስፋፋ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ መሆኑም ተመልክቷል
No comments:
Post a Comment