ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች እየተባባሰ ባለው የድርቅ አደጋ ዕድሚያቸው ከአምስት አመት በታች የሆነ ከ300 ሺ በላይ ህጻናት በአስከፊ የምግብ እጥረት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን የተባበሩት መንግስት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ገለጸ።
የአለም ባንክ በበኩሉ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ እያጋጠማት ያለው ኢትዮጵያ አደጋውን በዘላቂነት መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ማተኮር እንዳለበት አሳስስቧል።
አዲስ ተከስቶ ባለው በዚሁ የድርቅ አደጋ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች ከፍተኛ የምግብና የውሃ እጥረት አጋጥሟቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።
ባለፈው አመት የተከሰተው ይኸው የድርቅ አደጋ በመባባስ ላይ መሆኑን ተከትሎ 5.6 ሚሊዮን የነበረው የተረጂዎች ወደ 7.7 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶ በጋራ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የድርጅቱ የህጻናት መርጃ ተቋም በበኩሉ 303ሺ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆነ ህጻናት በአስከፊ የምግብ እጥረት ምክንያት የአካልና የጤና ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ አስታውቋል።
ድርጅቱ የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ እያካሄደ ላለው የሰብዓዊ ስራ የአውሮፓ ህብረት በዩኒሴፍ በኩል ተግባራዊ የሚሆን የሶስት ሚሊዮን ዩሩ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል።
መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሃገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመታደግ የ948 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ድጋፍ ጥሪን ቢያቀርቡም፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለጥሪው በቂ ድጋፍ አለማድረጉ ሲገልፅ ቆይቷል። የአለም ባንክ በበኩሉ ድርቁን ለመታደግ ለሚደረገው ጥረት የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ረቡዕ አስታውቆ፣ ሃገሪቱ በተደጋጋሚ እየደረሰ ላለው አደጋ ዘላቂ መፍትሄን ማፈላለግ እንዳለበት መስክሯል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2003 አም ጀምሮ በኢትዮጵያ አምስት ከፍተኛ የድርቅ አድጋ መከሰቱን ያወሳው ባንኩ ይኸው ክስተት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቂ ምክንያት ነው ሲል ገልጿል።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በመባባስ ላይ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊለወጥ ይችላል ሲል የተለያዩ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲያሳስቡ ቆይተዋል። የድርቁን አደጋ ተከትሎ በተከሰተ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ሰዎች በመሞት ላይ ቢሆኑም መንግስትም ሆነ የእርዳታ ድርጅቶች የሟቾችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በተለያዩ ቀበሌዎች በመሰራጨት ላይ ያለውን የበሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር ከ1ሺ በላይ የጤና ባለሙያዎች እንዲሰማሩ የተደረገ ሲሆን፣ ችግሩ አሁንም ድረስ ዕልባት አለማግኘቱ ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment