ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2009)
ከሳሽ አቃቤ ህግ ባለፈው አመት ከኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት ጋር በተያያዘ ተከስቶ የነበረውን ግጭት አነሳስተዋል ያላቸውን ሁለት ግለሰቦች በሽብር ወንጀል መክሰሱ ታውቋል።
ተከሳሾቹ ተፋ መልካ እና ከድር በዳሱ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆን፣ በበዓሉ አከባበር ወቅት ከሃገር ሽማግሌዎች ድምፅ ማጉያን በመቀማትና ሁከት በማነሳሳት ለ55 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል ተብለዋል። ከሳሽ አቃቤ ህግ ሁለቱን ተከሳሾች የሽብር ወንጀል ድርጊት መፈጸም የሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል።
ሁለቱ ተከሳሾች ከኢሬቻ በዓል አከባባር ጋር ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ምክንያት ናቸው ተብሎ ክስ ሲመሰረትባቸው የመጀመሪያዎቹ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
በበዓሉ አከባበር ወቅት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሲባል በስፍራው የነበሩ የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑን የበዓሉ ታዳሚዎች በወቅቱ ሲገልጹ ቆይቷል።
የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ ዕርምጃ ወስደው እንደነበር እማኝነት የሰጡ ታዳሚዎች፣ ከግጭቱ ለማምለጥ የሞከሩ በርካታ ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ህይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በወቅቱ 55 ሰዎች መሞታቸውን ቢገልፁም የተለያዩ አካላት የሟቾች ቁጥር ከ100 የሚበልጥ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በኢሬቻ በዓል ወቅት የተፈጸመውን ይህንኑ የሞት አደጋ ተከትሎ መንግስት በጥቅምት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መድረጉ ይታወሳል።
መንግስት በበዓሉ አከባበር ወቅት የጸጥታ አባላት በጥይት የገደሉት ሰው የለም በማለት ማስተባቢያን ቢሰጥም ከአደጋው የተረፉ ሰዎች መኖራቸውን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል።
በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የተፈጸመውን ይህንኑ ግድያ ተከትሎ በርካታ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል።
ይሁንና በተቃውሞው ስጋት ያደረበት መንግስት ድርጊቱን ለመቆጣጠር ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ አዋጁ ለአራት ወር እንዲራዘም ተደርጓል።
የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ ከ 24 ሺ በላይ ሰዎች ለእስር ተዳርገው ቢለቀቁም ወደ አምስት ሺ የሚሆኑ ክስ ይመሰርትባቸው ተብሏል።
አዋጁን የሚቆጣጠረው ኮማንድ ፖስት በአምስት ሺ ሰዎች ላይ ክስ ይመሰረታል ቢልም ክሱ መቼ እንደሚመሰረት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት አዋጁ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሆኗል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment