Monday, May 1, 2017

የአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ በሸንኮራ እጥረት ተከትሎ ምርቱን አቋረጠ

ኢሳት (ሚያዚያ 23 ፥ 2009)

የአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ ያጋጠመውን የሸንኮራ አገዳ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ ምርቱን ሙሉ ለሙሉ አቋረጠ።

ከ2007 አም ጀምሮ ስራውን በከፊል የጀመረው ፋብሪካው ችግሩን ለመቅረፍ በግንባታው ላይ ከሚገኝ ግድብ ውሃን በመጥለፍ የሸንኮራ አገዳ ለማምረት ቢሞከርም በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ጥረቱ ሳይሳካ መቅረቱን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ካባ መርጋ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ለዚሁ ፋብሪካ አገልግሎት አንዲሰጥ የታሰበ የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ መቅረቱ ታውቋል።

የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት እስኪሰጥ ድረስ የሸንኮራ አገዳ በዝናብ ለማምረት ጥረት ቢደረግም የተገኘው ምርት አነስተኛ መሆኑን የፋብሪካው ሃላፊዎች አስረድተዋል።



በኦሮሚያ የውሃ ስራዎች በ2003 አም ተጀምሮ የነበረው ግድብ በተያዘው አመት ስራው ይጠናቀቃል ቢባልም የግድቡ ግንባታ 48 በመቶ አካባቢ ብቻ መድረሱንም ለመረዳት ተችሏል። የፋብሪካው ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለዚሁ ግንባታ 2.6 ቢሊዮን ብር መድቦ እንደነበር ታውቋል።

ይሁንና የግድቡ ግንባታ በስድስት አመታት ውስጥ ከግማሽ በታች ብቻ ሊጠናቀቅ መቻሉ ተጨማሪ በጀት ይጠይቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የባለፈው ሳምንት የተንዳሆና የከሰም ስኳር ፋብሪካዎች ተመሳሳይ የሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት አጋጥሟቸው ስራቸው መስተጓጎሉ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የተንዳሆን ስኳር ፋብሪካ ከሁለት አመት በፊት ስኳርን ለውጭ ሃገር ገብያ ያቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም ችግሩ እስከቀጣዩ አመት ድረስ ቀጣይ እንደሚሆን የፋብሪካው ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ይኸው ከረጅም አመት ግንባታ በኋላ ወደስራ መግባት ያልቻለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በስራ ላይ ለሌሉ 1ሺ 577 ሰዎች ደመወዝ እየከፈለ መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከቀናት በፊት ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

ባለፈው ሳምንት በስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች የተመራ የልዑካን ቡድን ሃገሪቱ በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ጋር በተገናኘ ያጋጠማትን ችግር መቅረፍ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ለመምከር በህንድ ጉብኝት እያደረጉ መሆኑን መዘገቡም ይታወሳል። መንግስት ከቻይንና ከህንድ መንግስታት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ብድርን በመውሰድ 10 የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት ከአምስት አመት በፊት እቅድ መንደፉ አይዘነጋም።

ይሁንና ሃገሪቱ ስኳር ላኪ ሃገር ያደርጋሉ ተብለው የነበሩት የስኳር ፋብሪካዎች በመንግስት ላይ ተጨማሪ ኪሳራ እያስከተሉ እንደሚገኝ የመንግስት አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ፋብሪካዎቹ ወደ ስራ ባይገቡም መንግስት ሲወስድ የቆየው የብድር መክፈያ ጊዜ መቃረቡም ተመልክቷል። በሃገሪቱ ከፍተኛ የስኳር እጥረት በመኖሩ ምክንያት ከውጭ ሃገር ስኳር በመግባት ላይ መሆኑም ታውቋል።


No comments:

Post a Comment