Monday, June 27, 2016

በረሃብ የተጎዱ ዜጎች የእርዳታ አሰጣጡን አሰራር ነቀፉ

ሰኔ  ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በርሃብ የተጎዱ ዜጎች የሚቀርብላቸው እርዳታ በቂ አለመሆኑና በአንዳንድ ቦታዎች እስከ 7 ሰአት ተጉዘው 14 ኪሎ እህል ለወር ይዘው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

በምስራቅ አማራ እርዳታ የሚያከፋፍሉት በአብዛኛው የህጻናት አድን ድርጅትና የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ( ዩ ኤስ አይ ኤድ) ሲሆኑ፣ ድጋፋቸው ያነጣጠረው በሴፍትኔት ለታቀፉ ተጎጂዎች ነው።
እርዳታው በየወሩ የሚሰጥ ሲሆን  ለአንድ ሰው 14 ኪሎ ግራም ይሰፈርለታል፡፡ በዚህ አገልግሎት ላይ ቀለብ የሚሰፈርላቸው በሴፍቲኔት ምግብ ለስራ ላይ ለሚሳተፉ ብቻ ሲሆን፣ በርካታ እርዳታ ፈላጊ ወገኖች በተለይ ከብት ካላቸው አይስተናገዱም፡፡ “ከብቶቻችሁን ሸጣችሁ ተጠቀሙ እንደሚባሉ ተረጅዎች ይናገራሉ።

ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል ወይዘሮ በላይነሽ ንጉሴ አንዱ ናቸው። ወይዘሮ በላይነሽ የመስማትና የመናገር ችግር ሲኖሩባቸው በተመሳሳይ ልጆቻቸውም የአካል ጉዳተኞች መሆናቸውን ይናገራሉ።
በተለይ አንደኛው ልጃቸው በመታመሙ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ወልዲያ ሆስፒታል ልከውታል።  አንድ ሺ ብር ተበድረው ልጃቸውን ሆስፒታል የላኩት ወይዘሮ በላይነሽ በዕድሜያቸው የገፉ አቅመ ደካማ ቢሆኑም ሳይሰሩ የእርዳታ ቀለብ እንደማይሳጣቸው ስለተነገራቸው በደካማ ጉልበታቸው ለመስራት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
በየወሩ ቀለባቸውን ይዘው ለመሄድ ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸው የሚናገሩ ተጎጂዎችም አሉ፡፡የእርዳታ እህሉን ወደ ተጎጂዎች አካባቢ ለማድረስ የእህል መጋዝን የለም በመባሉ ለሰባት ሰዓት ተጉዘውና ከአራት ቀን በላይ ተጉላልተው እርዳታ የሚሰፈርላቸው  ተጎጂዎች፣  ሰሞኑን ወደ አንዳንድ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አንሄድም በማለት የወር ቀለባቸውን ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡
መንገዱ አቀበትና ቁልቁለት ያለው ስቃይ የበዛበት መሆኑን የሚናገሩት ተጎጂዎች ከቤታቸው አስረው ሚያመጡት ቀለብም በጸሃይ እና ሙቀት ወዲያውኑ እንደሚበላሽ ተናግረዋል፡፡
“ይህን ያህል ለፍተንና ወጪ አውጥተን ለመውሰድ ብንመጣም ከምናገኘው ቀለብ ይልቅ በእርዳታ ማከፋፈያው ከተማ ለማደሪያ ክራይና ምግብ ወጪ በመዳረጋችን እየተጎዳን ነው” በማለት ወደ ምግብ  ማከፋፈያው ቦታ ላለመሄድ ወስነዋል፡፡ በቆቦ ዙሪያ የሚገኙት ተጎጂዎች ደግሞ በአብዛኛው ስርዓት ባለው መልኩ ዓመቱን ሙሉ ምንም ዕርዳታ አልወሰዱም ፡፡አልፎ አልፎ መንግስት በሚልክላቸው ውስን ዕርዳታ ምክንያትም ብዙውን ጊዜ አለመስማማት እንዳለና ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ሰዎች እርዳታውን እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
የእርዳታ እህል ቢመጣም እርስበርስ እንዲጣሉ ከማድረግ ውጭ ብዙም እንዳላገዛአቸው ገልጸዋል፡፡ የሚመጣው የዕርዳታ እህል ለአንዳንድ ድሃ ከተሰጠ በኋላ ቀሪው ተረጅ ያለቀለብ ወራትን እንዲገፋ መደረጉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ መንግስታዊ ቡድኑ ቀሪውን እህል የት እንደሚደያርሰው እንደማያውቁ ይናገራሉ።
ህብረተሰቡ የዕርዳታው እህል ሳይደርሰው ሲቀር ከአካባቢው አመራሮች ጋር እርስበርስ በመጋጨት ላይ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በቀበሌያቸው ከሚገኙ ችግረኞች ከአራት አንዱ እንኳን የዕርዳታ እህል የማያገኝበት ጊዜ እንዳለ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ዘንድሮ ዝናቡ እያካፋ በመሆኑ ትንሽ እርጥብ ማየታቸውን የሚናገሩት ተጎጂዎች የሚበቅለው እህልም አነስተኛ በመሆኑ በአብዛኛው ለዘር በማዋል አመቱን ሙሉ በችግር እንደሚያሳለፉ  አክለዋል።

No comments:

Post a Comment