ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አርበኞች ግንቦት ሰባት ከትናንት በስቲያ በጀርመን ፍራንክፈርት የተሳካ ህዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በተገኙበት አካሂዷል። ስብሰባውን ለመቃወም የገዢው ስርዓት በኤምባሲው አማካይነት በመላ አውሮፓ የሚገኙ ደጋፊዎቹን ሰልፍ እንዲወጡ የጠራ ቢሆንም በሰልፉ ላይ ሊገኙ የቻሉት ግን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎቹ ሲሆኑ ስብሰባውን ለመታደም የተገኙ ወገኖች በጣም በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ አዳራሹ ሞልቶ ብዙዎች መግባት ሳይችሉ ለመመለስ ተገድደዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአውስትራሊያ በካንቤራና በሜልቦርን ህወሃት የጠራው የድጋፍ ስብሰባ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባሰሙት ጠንካራ ተቃውሞ ስብሰባው በአውስትራሊያ ፖሊስ እንዲሰረዝ ተደርጓል። የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱ ፤ የሶማሌው ክልል ፕሬዘዳንት አብዲ መሃመድ ኡመር እንዲሁም የኦሮምያ ክልል ፕሬዘዳንት ሙክታር ከድር እና የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ ያለው አባተ በሜልቦርን ከተማ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
በአውስትራሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሶስቱ ክልል ባለስልጣናት አውስትራሊያ እንደሚገቡ አስቀድሞ መረጃ የደረሳቸው ሲሆን፣ ተቃዋሚዎቹ ከአውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ሲከታተሉዋቸው ቆይተዋል። ቅዳሜ ጁን 11 ፣ 2016 በካምቤራ ከተማ ሊካሄድ የነበረው የመጀመሪያው ስብሰባ ከሲድኒ ከተማ በሄዱ ኢትዮጵያውያን እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን ፣ በማግስቱ በሜልቦርን ከተማ ሊደረግ የነበረውም ስብሰባ በተመሳሳይ መንገድ ተቋርጧል።
ኢምባሲው ጥሪ ከተደረገላቸው የህወሃት ደጋፊዎች በስተቀር ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዳይገኙ ለማድረግ ፣ የስብሰባውን ቦታ ለትግራይ ኮሚኒቲ አባላት ብቻ በስልክ ለማስታወቅ ተገዷል። በጥሪ ደብዳቤው ላይ በተጠቀሰው ቦታ ከጥቃቱ 12 ሰአት ጀምሮ የተገኙት ኢትዮጵያውያን፣ በስፍራው ምንም ስብሰባ እንደማይካሄድ ሲያውቁ፣ ሌሎች የስብሰባ ቦታዎችን ማፈላለግ ግድ ሆኖባቸዋል።
ተቃዋሚዎቹ ስብሰባው ከከተማው ውጭ መዘጋጀቱን መረጃ እንደደረሳቸው ወደ አካባቢው ተጉዘው ፣ የህወሃት ደጋፊዎች ያልጠበቁት ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል። ከ50 እስከ 60 የሚሆኑ የህወሃት አባላት በአውቶቡስ ተሳፍረው ወደ ስብሰባ አዳራሹ ለመግባት ሲሞክሩ በአካባቢው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን አጠናክረው በመቀጠላቸው፣ የአውስትራሊያ ፖሊስ በመሃል ገብቶ ውጥረቱን ለማርገብ ሞክሯል።
ተቃዋሚዎች “ አውስትራሊያ የወንጀለኞች ዋሻ አትሆንም፣ ስብሰባው ይሰረዝ “ የሚሉና ሌሎችም መንግስትን የሚያወግዙ መፈክሮችን በከፍተኛ ስሜት ሲያሰሙ የዋሉ ሲሆን፣ ፖሊስ ስብሰባው ቢቀጥል ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል በማወቁ ፣ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት እንዲቋረጥ አድርጓል።
የሶስቱ ክልል ፕሬዚዳንቶች በአውስትራሊያ ከፍተኛ ገንዘብ ለመሰብሰባ እንዲሁም የፖለቲካ ስራ ለመስራት አልመው ቢመጡም ሳይሳካላቸው የቀረ ሲሆን፣ የአውስትራሊያ ሚዲያዎችም ድርጊቱን ቀርጸው ለህዝብ አስተላልፈዋል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወደ ውጭ ለቅስቀሳ በሚሄዱበት ጊዜ በተደጋጋሚ ተቃውሞ እየደረሰባቸው እቅዳቸው ቢከሽፍም፣ አንድም ቀን የችግሩ ምንጭ ምንድነው ብለው በመጠየቅ፣ በውጭ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ለመመለስ ሲሞክሩ አልታዬም። አብዛኛውን በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ቤት እና መሬት በመስጠት በጥቅም ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረትም የጠበቁትን ያክል ድጋፍ አላስገኘላቸውም።
No comments:
Post a Comment