Wednesday, June 29, 2016

ከመከላከያ ሰራዊት ተሰናብተው በየከተማው የሚገኙ ዜጎች ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እሁድ ሰኔ 19/2008 በብቸና ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የተመላሽ ሰራዊት አባላት በደረቅ ቆሻሻ ተሰብስበው በመሰማራት ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ቢሆኑም የመንግስት አመራሮች ግን ከእርዳታ ይልቅ ጥላቻ እያሳዩዋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ መከላከያ ሰራዊቱ እንዲገቡ በርካታ እንክብካቤና የማስመሰያ ቅስቀሳ ተደርጎላቸው እንደተሸኙ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች በተቀናሽነት ሲመለሱ ግን አግባብ ባልሆነ አቀባበል እንደተቀበሉዋቸው ይናገራሉ፡፡
በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ መከራና ስቃይ ሲያዩ ቆይተው ለሃገራቸው ምድር ቢበቁም ከወረዳ አመራሮች የጠበቃቸው በጥላቻ የተሞላ መስተንግዶ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፤ ከሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ በመነፈጋቸው በችግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ሰሞኑን በመላ ሃገሪቱ በሚካሄዱ የመከላከያ ሰራዊት ምልመላዎች ከፍተኛ ደመዎዝ ፣ልዩ ልዩ የሙያ ስልጠና እንደሚሰጥና ከተማ ውስጥ መኖር የሚያስችል ዕድል እንዳለ በመንገር ቅስቀሳ ቢካሄድም አብዛኛው ወጣት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ቅስቀሳ በማድረግ እንዲያስመዘግቡ ጥብቅ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜናም ከባድ መሳሪያዎችንና ወታደሮችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች መብራት መጥፋቱን ተከትሎ በምሽት ወደ ትግራይ ማቅናታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment