ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት የጸረሽብር ህግን በመጠበቀም በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ በግል መገናኛ ብዙሃን፣ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች እንዲሁም በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ወከባና እንግልት እንዲያቆም የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማህበር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ሃይለማሪያም መንግስት እየወሰደ ያለው አፈና በኦሮሚያ ተቃውሞ እንዲስፋፋ አስተዋጽዖ አድርጓል ሲሉ ዲፌንድ ዲፌንደርስ ለተባለው በምስራቅና በአፍሪካ ቀንድ ለሚሰራው ተቋም ተናግረዋል። በመሆኑም የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia (AHRE)) በመንግስት የተቀነባበረውን አፈና እንዲያስቆምና የታሰሩ የመንግስት ተቃዋሚዎችን እንዲያስፈታ ማድረግ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት ለማስቆም ያግዛል ብለዋል።
በቅርቡ በተቃዋሚዎች፣ ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተወሰደው የጸረሽብር ድርጊት ክስ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ነቀፋን የማይቀበል መሆኑን ማሳያ ነው ሲል ድርጅቱ በመግለጫው አክሎ ገልጿል።
አዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ተከትሎ በኦሮሚያ በተከሰተው ተቃውሞ፣ የጸጥታ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በማሰር በመቶዎች የሚቆጠሩትን ዜጎች ገለዋል ሲል ይኸው ድርጅት በመግለጫው አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው ተቃውሞን ተከትሎ ከየካቲት 2008 ጀምሮ በመንግስት ሃይሎች ከታሰሩት መካከል ዜጎች መካከል አብዛኞቹ በጸረሽብር ህጉ የተከሰሱ መሆናቸው ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። የነገረ ኢትዮጵያ ኤዲተር ጌታቸው ሽፈራው፣ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ፣ የኦሮሞ ፊዴራሊስት ኮንግሬስ ምክትል ዋና ጸሃፊ ደጀኔ ጣፋ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ጸሃፊ ጉርሜሳ አያና እና የዜና አርታኢ እና ዘጋቢ ፍቃዱ ምርቃና በጸረሽብር ህግ ከተከሰሱት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።
በጸረሽብር ህግ የተከሰሱት እነዚሁ ዜጎች የተወሰኑት ያለምንም የፍርድ ሂደት በተለያዩ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ እንደሆነ ዲፌንድ ዲፌንደርስ (defend defenders) በሚባል ድረገጽ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።
የአሜሪካንን መንግስት ጨምሮ ተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ አገሮች፣ እና የፓርላማ አባላት የኢትዮጵያ መንግስት በጸረሽብር ህግ ያሰራቸውን ዜጎች እንዲለቅ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም፣ አሻፈረኝ እንዳለ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ዋቢ አድርጎ በድረ-ገጹ ላይ የሰፈረው ሪፖርት ያስረዳል።
የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ የDefend Defenders ስራ አሲያጅ የሆኑት ሃሰን ሽሬ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የአለም ማህበረሰብ የኢትዮጵያን መንግስት ድርጊት ማውገዝ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል። የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ከንግግር የዘለለ ዕርምጃ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ መውሰድ አለበት ሲሉ የተለያዩ ድርጅቶችም ጠይቀዋል።
No comments:
Post a Comment