ሰኔ ፩(አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ድርጅት ፣ ኦብነግ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የመከላከያ ሰራዊት ግንቦት28፣ 2008 ዓምበጋሻሞ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ጃማ ዱባብ መንደር ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት 51 ሲቪሎች ተገድለዋል። ጦሩ ፊት ለፊት ባገኛቸው ዜጎች ላይ በጭፍን መተኮሱን የገለጸው ኦብነግ በጥቃቱ ህጻናት፣ ሴቶችና ሽማግሌዎች ተገድለዋል። ጦሩ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ነዋሪዎቹ መስጊድ በመግባት ራሳቸውን ለማትረፍ ጥረት ቢያደርጉም፣ ሰራዊቱ ግን መስጊድ ድረስ በመግባት እንደገደላቸው ድርጅቱ አስታውቋል። ሰራዊቱ መንደሩን በማቃጠል፣ የነዋሪዎችን ንብረት አውድሟል።
በጥቃቱ ቆስለው ለማምለጥ የቻሉ ሲቪሎች በየአካባቢው ተደብቀው እንደሚገኙ የገለጸው ኦብነግ፣ በርካታ ህጻናትና አዋቂዎች እስካሁን አለመመለሳቸውን ገልጿል። ሰራዊቱ 10 የአገር ሽማግሌዎችን አፍኖ መውሰዱንና ያሉበት አለመታወቁንም ግንባሩ ገልጿል።
ድርጊቱ መንግስት ከአካባቢው ህዝብ ምንም አይነት ተቃውሞ እንዳይነሳበት ለማድረግ የወሰደው እርምጃ ነው የሚለው ኦብነግ፣ በአሁኑ ሰአትም ተጨማሪ ሰራዊት ወደ አካባቢው በመላክ አጎራባች ቀበሌዎችን ወሯል ብሎአል። ከሁለት ወራት በፊት የመከላከያ ሰራዊቱ በዋርዴር ዞን በጋላዲ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ በዳሃዲሲሂር እና ጋጣንዳሃሌ መንደሮች በፈጸመው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን፣ በየካቲት ወር ደግሞ የመከላከያ ሰራዊቱ ከልዩ ሚሊሺያው ጋር በመሆን በላባባር መንደር አካባቢ ያሉ ከ300 ያላነሱ ሰዎችን በማጥፋት አካባቢውን ለካሉብ ጋዝ ማውጫ ስራ አውሎታል ሲል ግንባሩ አስታውቋል። ባለፈው አመት መጨረሻ በቡር ኡኩር፣ ፈርፈር፣ በለደወይን እና ሁዱር አካባቢዎችም ተመሳሳይ ጥቃቶች ተፈጽመው ዜጎች ተገድለዋል።
በኦጋዴን፣ በኦሮምያ በአጠቃላይ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተነሱትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማዳፈን በሚል አገዛዙ ከፍተኛ ወንጀል ከፈጸመ በሁዋላ አሁን ደግሞ ፊቱን በድንበር አካባቢ ወደ ሚገኙ ነዋሪዎች ማዞሩን በተለይም በሶማሊና ኬንያ ድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ገልጿል። ኦብነግ ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ አውግዞ ፣ ሁሉም ህዝቦችና በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ፓርቲዎች እንዲሁም የአለማቀፍ ማህበረሰብ በጋራ ሊያወግዙት ይገባል ብሎአል። ለተጎዱ ዜጎችም አፋጣኝ እርዳታ እንዲደርሳቸው ጠይቋል።
በኦነግ በኩል የቀረበውን መግለጫ በተመለከተ የአህአዴግ አገዛዝ እስካሁን የሰጠው መልስ የለም።
No comments:
Post a Comment