ሰኔ ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር የደቡብ ሱዳን የሰላም አስከባሪ ጦር ሰላማዊ ዜጎችን ከለላ መስጠት አልቻለም ተባለ።
በእርስበርስ ጦርነት የምትታመሰው አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን በማላካል ከተማ ውስጥ እልቂት ሲፈፀም በስፍራው የነበሩት የሰላም አስከባሪ ጦር አባላት የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እንዳልቻሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምርመራ ቡድን ጥናት ሪፓርት አስታውቋል።
ቁጥራቸው 48 ሽህ በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች በደቡብ ሱዳን ጦር አባላት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ 40 የሚሆኑት ሲገደሉ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በግዳጅ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። የእርስበርስ የጎሳ እልቂቱን ተከትሎ የነዋሪዎች ቤት በእሳት ጋይተዋል ፣አናሳ ጎሳዎች ላይ የዘር እልቂት ተፈጽሟል። ይህን የመሰለ ዘግናኝ ግፍ ሲፈፀም የሱዳን መንግስት ጦር አባላት ተሳታፊ እንደነበሩም ሪፓርቱ አመልክቷል።
በደቡብ ሱዳኗ ማላካል ከተማ ውስጥ እልቂት ሲፈፀም በስፍራው የነበሩት የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ አባላት ስፍራውን ትተው መሄዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወታደራዊ ባለስልጣን ገልፀዋል። ባለስልጣኑ የሩዋንዳ ጦር አባላትም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ለሰላማዊ ዜጎችን ከለላ ከመስጠት ይልቅ የአየር ማረፊያውን ለደቡብ ሱዳን ጦር አስረክበው ለቀው መሄዳቸውን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪ የሆኑት ማት ዌል ፣ የምርመራ ጥናት ሪፓርቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የግጭቱን መንስኤ ለጸጥታው ምክር ቤት እንዲያቀርብ መነሻ ይሆነዋል ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ መጠለያዎች አቅራቢያ የሰላማዊ ዜጎች ግድያና የመኖሪያ ቤቶች የእሳት ቃጠሎ ሲፈጸም የሰላም አስከባሪ ጦር አባላት ምላሽ የሰጡት ዘግይተው መሆናቸውንና ምላሻቸውም ፋይዳ ቢስ እንደነበር የምርመራ ጥናት ሪፓርቱ አብራርቷል። ሁለት የሰላም አስከባሪ ሰራተኞችን ጨምሮ 18 የድርጅቱ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችም መገደላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment