Friday, June 3, 2016

በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የ288 ተማሪዎች መኖሪያ ዶርሚተሪ ተቃጠለ



ግንቦት ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  መንስኤው በውል ባልታወቀ ሁኔታ በተነሳው ቃጠሎ ቀደም ብሎ ከመቃጠል የተረፉት ሁለቱ ብሎኮች በእሳት ጋይተዋል። ቀደም ብሎ በደረሰው ቃጠሎ የ587 ተማሪዎች መኖሪያ የሆኑ 5 ህንጻዎች ወድመው ነበር።

ለሳምንታት ትምህርት ያቋረጡት  የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ካልጀመሩ ግን ከዩኒቨርስቲው እንደሚባረሩ ተነግሯቸዋል። የፌደራል ፖሊሶች ግቢውን ለቀው ለመውጣት የሚሞክሩ ተማሪዎችን ሰነዶች ሲቀሙ መታዬታቸውን ወኪላችን ገልጿል። በዩኒቨርስቲው የተጀመረው ተቃውሞ በኦሮምያ የተነሳው ተቃውሞ አካል ነው።

በሌላ በኩል በሃረር ከተማ የሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ዛሬ በማድረግ ላይ ባሉት ስብሰባ፣ ወጣቶቹ “በሃረሪ ክልል የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ላይ የባርነት ስርዓት እየተተገበረ ነው፣ ሁለተኛ ዜጋ እድጋችሁናል፣ ወጣቱን ስራ አሳጥታችሁዋል፣ ፍትህ የለም፣ መልካም አስተዳደር የለም” በማለት ወጣቶቹ ጠንካራ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
ወጣቶቹ “ እናንተ የችግሩ አካል ሆናችሁ መፍትሄ ልትሰጡ አትችሉም፣ የምትጠሩት ስብሰባ በህዝብ ላይ ለመቀለድ እና እኛን ለመታዘብ እንዲሁም አልበቃችሁም ብላችሁ ሌላ ጭቆና ልታደርሱብን ነው” በማለት ተናግረዋል። በክልሉ ያለው የህዝብ ብሶት እየጨመረ መምጣቱን ስብሰባውን የተከታተለው ወኪላችን ገልጿል። ከሁለት ቀናት በፊት የክልሉ ፕሬዚዳንት ከነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባም ተመሳሳይ ጠንካራ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። ፕሬዚዳንቱ በሙስናና በመልካም አስተዳዳር የተዘፈቁ ጠበቆችን፣ ፖለሶችንና ሰራተኞችን ማባረራቸውን በመግለጽ የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ ቢሞክሩም፣ ህዝቡ ግን የተጠራቀመ ብሶቱን ከመግልጽ አልተቆጠበም ነበር።
ከክልሉ ዜና ሳንወጣ ዛሬ ቀን 7 ሰአት ተኩል አካባቢ በሃረር አንደኛ መንገድ ላይ የቻይና የመንገድ ስራ ድርጅት ንብረት የሆነ ሬንጅ የሚረጭ ቦቴ መኪና ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል። የእሳት አደጋ መኪና ተጠርቶ ቢመጣም፣ መኪናው ምንም ውሃ ሳይዝ ቦታው ላይ ተገኝቷል። መኪናው ውሃ ለመቅዳት መመለሱን የገለጸው ወኪላችን፣ ህዝቡ በአፈርና በውሃ ተረባርቦ እሳቱን ማጥፋቱንና መኪናው ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጿል። የቃጠሎው መንስኤ በትክክል አለመታወቁንም ገልጿል።  አሁን በደረሰን ዜና ደግሞ የ 1ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሮዋቸዋል ።

No comments:

Post a Comment