Friday, June 3, 2016

በድርቁ ምክንያት በስደት እንደወጡ የቀሩ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ አለማወቃቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

ግንቦት ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  የሃገሪቱን አብዛኛውን የእርሻ ስራ ያከናውን የነበረው ወጣት ኃይል በረሃቡ ምክንያት ስደት እንደወጣ መቅረቱ ወላጆችን እያሳሰባቸው መሆኑን የአማራ ክልል የድርቁ ተጎጂዎች ተናገሩ፡፡

በየቀያቸው ቆይተው ድርቁን ለመቋቋም ያልቻሉ አምራች ኃይሎች ወደ ተለያዩ ጠረፍ ከተሞችና በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ተሰደዋል፡፡ህይወታቸውን ለማቆየት በሚያደርጉት ሩጫ በበርሃ በሽታዎችና በተለያዩ አደጋዎች የመሞታቸው መርዶ እንጅ የመመለሳቸውን የምስራች አለመስማታቸው የቀን ከቀን ክስተት መሆኑ ወላጆች  ይናገራሉ፡፡

ወደ ስደት የሚሄዱትን ወገኖች የገዥው መንግስት አመራሮች እየተመለከቱ ምንም ዓይነት እርዳታም ሆነ እገዛ ሳያደርጉ በዝምታ መመልከታቸው እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል። በተቃራኒው የአካባቢው አመራሮች “እስካሁን ድረስ በምግብ ችግር የሞተም ሆነ ቀየውን ለቆ የሄደ አርሶ አደር የለም ነገር ግን የምግብ ችግር በስፋት አለ፡፡” በማለት የአካባቢው አመራር እርስ በርሱ የሚቃረን ምላሽ ሲሰጡ ይሰማሉ።
ገንዘብ ያላቸው ተጎጂዎች ጉዳቱ በተከሰተበት ቀያቸው ሆነው ገንዘቡ ምንም ሊያግዛቸው ባለመቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀያቸውን በመልቀቅ ወደ ከተሞች በመሄድ እንደሌሎች ወገኖቻቸው እጃቸውን ለእርዳታ መዘርጋታቸው እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡ “ልጄ ምን ላይ ወድቆ ይሆን ?” “ልጄ ምን ላይ ወድቃ ይሆን?”የሚሉት በድርቅ በተጎዱ ቀበሌዎች የሚገኙ አቅመ ደካማ ወላጆች ዓመቱን በሙሉ በጭንቀት አንዳሳለፉ  አጥጋቢ እርዳታ እንዳላገኙ ተጎጂዎች ይናገራሉ።
ከረሃብና ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በእርዳታ ኑሮአቸውን ለመግፋት ተገደዋል። የአለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ እርዳታ በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ ተጎጂዎች ግን  የሚሰጠው እርዳታ በቂ አለመሆኑን እየገለጹ ነው።

No comments:

Post a Comment