መስከረም ፳ (ኅያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲወዛገቡ የቆዩት የአፋር ክልል ባለስልጣናት ፣ የህወሃት ድጋፍ ያለው አቶ ስዩም አወልና የአቶ አሊ ሴሮ ቡድን በአሸናፊነት ከወጣ በሁዋላ፣ ላለፉት 20 አመታት የጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ሃላፊ ሆነው የሰሩት አቶ ስዩም አወል አሁን ከያዘው ስልጣን በተጨማሪ የክልሉ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
በተቃራኒ ጎራ የተሰለፈውና የተማረውን ሃይል አካቷል የተባለው የአቶ ጠሃ ቡድን በአቶ ስዩም ቡድን ተመትቷል። አቶ ጠሃ ከፓርቲው ሊቀመንበርነትና ከስራ አስፈጻሚ አባልነት ተሰናብቷል።
ከፌደራል መንግስት የተወከሉት ሁለት የህወሃትና አንድ የብአዴን ባለስልጣናት ፣የአብዴፓን መተዳደሪያ ደንብ በመጥቀስ የአቶ ስዩምን ሹመት ሲቃወሙ የነበሩትን የፓርቲው አባላት ታማኝነታቸውና ድጋፋቸውን ለአቶ ስዩም እንዲገልጹ ሲያግባቡ ሰንብተዋል።
ውዝግቡን ተከትሎም ህዝቡ ተቃውሞውን መግለጽ ጀምሯል። በሰሜን አፋር በዳሎል ወረዳ ህዝቡ በዚህ መንግስት አንተዳደርም በማለት ተቃውሞውን እየገለጸ ነው።
የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊው አቶ ስዩም አወል፣ አቶ ሙሃመድ አምበጣና አቶ እስማኤል አሊሴሮ የህወሃት ታማኝ የክልሉ ባለስልጣናት ናቸው።
አቶ ጠሃን በመደገፍ አቶ አህመድ ሱልጣን፣ አቶ አወል አርባና አቶ ሙሃመድ ኡስማን ከጎናቸው ቆመዋል። ሁለቱ ቡድኖች ሲያደርጉት የነበረው ውዝግብ ክልሉ ለ3 ወራት ያክል በሞግዚት አስተዳደር እንዲመራ ተደርጓል። 39 መቀመጫ ባለው የድርጅቱ ምክር ቤት አቶ ጠሃ መሃመድ 16 ድምጽ ሲያገኙ ፣ የእሳቸውን ሹመት የሚቃወሙት የአቶ አሊ ሴሮ ደጋፊዎች ደግሞ 20 ድምጽ አግኝተዋል። ሶስት ሰዎች በስብሰባው ባለመገኘት ድምጽ አልሰጡም። የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ የድርጅቱ ሊቀመንበር ስልጣኑን የሚያጣው በ2/3ኛ ድምጽ ነው የሚል ሲሆን፣ በዚህ ስሌት መሰረት አቶ ጠሃን ለማውረድ 26 የተቃውሞ ድምጽ ቢያስፈልግም፣ የህወሃት ባለስልጣናት ህጉን በመጣስ አቶ ጠሃ በ20 ድምጽ ከ4 ወራት ሹመት በሁዋላ ከስልጣን እንዲወርድ አድርገዋል። በእርሳቸው ምትክ አዲስ ሰው ለመሾም እንቅስቃሴ መጀመሩንና በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት አዲሱ ሰው እንደሚሾም ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment