መስከረም ፳፮ (ኅያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ኬንያ ሲገቡ መንገድ ላይ ያዝኳቸው ያለውን አስራ አራት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የኬንያ ፖሊስ ይዞ ማቻኮስ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል።ስደተኞቹ የቀረበባቸውን ክስ ያልተቀበሉት ሲሆን የሃያ ሽህ ሽልንግ የገንዘብ ቅጣት ወይም የመቶሰላሳ ቀናቶች የእስር ቅጣት እንደሚበየንባቸውና ቅጣቱን ከከፈሉ በኋላ ወደ አገራቸው እንደሚላኩም ተገልጿል።
ስደተኞቹ በናይሮቢ ሞንባሳ አውራ ጎዳና በማቻኮስ በቹሙቪ የገበያ ማዕከል ውስጥ ባለፈው ወር የተያዙት ሲሆን፣ አካባቢው ሕገወጥ የአደንዛዥ ዕፅ፣ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችና የዝሆን ጥርስ የሚዘዋወርበት መሆኑንም የኬንያ የፀጥታ ሰራተኞች ገልፀው፣ ባለፈው ዓመትም በዚሁ ስፍራ 95 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ሲሞክሩ እንዲሁም በካሃዋ ግዛት ውስጥ አስራ ሁለት ኢትዮጵያን ቤት ውስጥ ተደብቀው መያዛቸውንም አክሎ ገልጿል።በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የሚገቡትን የሶማሊያ፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ ዜጎችን በማስተላለፍ ላይ የተሰማሩ የአገሪቱ ዜጎች እንዳሉም ፖሊስ አመልክቷል።
በሃምሌ ወር ላይ ሃያ አራት ሰደተኞችን የጫነ መኪና አደጋ ደርሶበት አንድ ሰው የሞተ ሲሆን ብዙ ተጓዦችም መቁሰላቸውንና ወደ ደቡብ አፍሪካ ሰዎችን በሕገወጥ በማዘዋወር የተሰማሩ ግለሰቦች በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ብቻ ከዘጠና ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ በላይ እንደሚያገኙ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም በጥናቱ አመልክቷል። ባለፉት አስራአምስት ዓመታት ውስጥ በየቀኑ ከሰላሳ በላይ ኢትዮጵያዊያን የሞያሌ ድንበርን አቋርጠው ኬንያ የሚገቡ ሲሆን ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ እንደሚኖሩ ይገመታል ሲል ታንዛኒያን ዲሳይድድ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment