ጥቅምት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃገሪቱ ከሚገኙ አምራች አካባቢዎች አንዱ በሆነው በየዓመቱ ከሰኔ እስከ ህዳር ወር ድረስ ከፍተኛ የሰራተኛ ቁጥር የሚያስተናግደው የምዕራብ አርማጮኾ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚገኙ የጤና ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን በጀት የክልሉ መንግስት ባለመመደቡ በየአመቱ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ የወረዳው የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች ተናገረዋል፡፡
በምዕራብ አርማጮኾ ወረዳ ያለው ነዋሪ አርባ አምስት ሽህ አካባቢ ነው በማለት የሚያስበው ገዢው መንግስት፣ በሕዝቡ ቁጥር አመታዊ በጀት ቢመድብም ፤ በተጨባጭ የሚታየው የሕዝብ ብዛት በእያንዳንዱ ቀበሌ በግማሽ መጨመሩን የሚገልጹት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የወረዳው ጤና አጠባበቅ አመራሮች፣ ወደ አካባቢው ለቀን ሥራ የሚመጡ ከሁለት እስከ ሶስት መቶ ሽህ የሚደርሱ ዜጎችን ጨምረው የህክምና አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንዳዳገታቸው ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው በሚከሰተው የወባ በሽታ በርካታ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች እንደሚታመሙ የሚገልጹት ባለሙያዎች ፤ አብዛኛውን መድሃኒት ለተንቀሳቃሽ ሰራተኞች ከተጠቀሙ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ የጤና ተቋማቱ ጎራ ሲሉ መድሃኒት በግል ከውጭ እንዲገዙ መደረጉ ግጭት ውስጥ እያስገባቸው መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በአካባቢው ለሚከሰቱ የተለያዩ አጣዳፊ በሽታዎችና እንደ ፖሊዮ ያሉ የዘመቻ ህክምናዎች ላይም ለወረዳው የሚታዘዝለት የበጀት መጠን በነዋሪው ትክክለኛ ቁጥር ሳይሆን ከዓመታት በፊት የክልሉ መንግስት በያዘው የቁጥር መረጃ በመሆኑ ባለሙያዎች ስራቸውን በአግባቡ ለመስራት የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን አመራሮቹ ይናገራሉ፡፡
በወረዳው በጤናው ዘርፍ ከሚያገለግሉት የመንግስት ሰራተኞች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት ባለሙያ ‹‹ የታካሚ በሽተኞች እና የመድሃኒት አቅርቦቱ ምጥጥን እኩል አይደለም ፡፡በዚህ ዙሪያ የክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ቢጠየቅም አጥጋቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ችግሩ ለዓመታት ተሸጋግሯል፡፡››ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለመድሃኒት የሚመደበው ዓመታዊ በጀት ለወረዳው ነዋሪ ህብረተሰብ ብቻ ታስቦ የሚሰጥ በመሆኑ በቀን በቀን የሚስተናገዱት እስከ መቶ ሃምሳ የሚደርሱት በወረዳዋ የእርሻ ቦታዎች የሚሰሩ ሰራተኞችን በማስተናገድ መድሃኒት ያለጊዜው እንደሚያልቅና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚማረሩ ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡
ባለሙያዋ አክለው እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ለመድሃኒት ግዢ የሚመድበው ገንዘብ የቀን ሠራተኞችን ያማከለ ባለመሆኑ በመድሃኒት እጥረት ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ተደጋጋሚ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ በመድሃኒት እጥረት ምክንያት በልዩ ልዩ ስብሰባዎች ጉዳዩን በመልካም አስተዳደር እጦት ጥያቄነት እያቀረቡ መሆናቸውን የሚገልጹት ባለሙያዋ፣ በአካባቢውም ሆነ በዞን ደረጃ በሚካሄዱ ስብሰባዎች የመድሃኒት እና የጤና ጣቢያዎች በጀት እንዲስተካከል በየጊዜው ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ባለመሰጠቱ ነዋሪው በችግር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምዕራብ አርማጮኾ ወረዳ ቀበሌዎች በመንገድ፣በመብራት፣በጤና በ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃና ስልክ አገልግሎቶች ዙሪያ ያለባቸውን ችግር ከአንድ ዓመት በፊት የክልሉ ርዕሰ መስተደድር የካቢኔ አባሎቻቸውን በመያዝ በአካባቢው በተገኙበት ጊዜ ጥያቄዎችን አቅርበው ቃል ቢገባላቸውም፣ እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸው የአካባቢውን ነዋሪ ያገለለና ህብረተሰቡን እንደ ዜጋ ያለመቁጠር አዝማሚያ የታየበት ነው በማለት በአብርሃጅራ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ገልጸው፤በአካባቢው የሚታየው ያለመረጋጋትም የገዢው መንግስት ለነዋሪው ከሚያሳየው ንቀት የመነጨ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment