መስከረም ፳፭ (ኅያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል መንገድ ስራ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚታዩ በርካታ የአሰራር ችግሮች ለከፍተኛ ሙስና ሊያጋልጡ እንደሚችሉ በመናገር በየጊዜው እንዲስተካከሉ ሰራተኛው ቢጠየቅም፣ ከዓመት ዓመት አለመቀረፋቸው በስርዓቱና አመራሮች እምነት እንዲያጡ እንዳደደረጋቸው የኦዲት ባለሙያዎች በዓመታዊው የሰራተኞች ስብሰባ ላይ ገልጸዋል፡፡
በባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ስር በሚገኙ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በተደረገ አጠቃላይ ምርመራ በፋይናንስ አስተዳደርና በግዢ አፈጻጸም ቀደም ብለው የታዩና አሁንም ያልተቀረፉ ችግሮችን በዝተዋል
።« አለመስራት አያስጠይቅም !! » የሚል መደምደሚያ ላይ የተደረሰ ይመስላል ያሉት ባለሙያዋ፣ የጥሬ ገንዘብ በመዝገብ አለመያዝ፣በየዕለቱ የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ የማይደረግ መሆኑና በየወሩ የባንክ ማስታረቂያ አለመሰራቱ፣ ከአንድ ወር በላይ ዕድሜ ያለው ተንጠልጣይ ሰነድ ወደ ተሰብሳቢ ሳይቀየር በገንዘብ ያዥ እጅ መገኘት ፣በቸክ ክፍያ ሲፈጸም በወጪ ማመሳከሪያ ሳይዘጋጅ ክፍያ መፈጸም፣ያለ አግባብ ውሎ አበል መክፈል፣በካዝና ማደር ከሚገባው ገንዘብ በላይ ጥሬ ገንዘብ በካዝና ውሰጥ መገኘት፣ለሰራተኞች በተንጠልጣይ ሰነድ የተሰጠ ክፍያ ሳይወራረድ በድጋሚ ቅድሚያ ክፍያ መስጠት፣ነዳጅ ስራ ላይ ሳይውል ሰነድ በማዘጋጀት እንዲወራረድ ማድረግ፣የትምህርት ማስረጃ ከግል ማህደር ጋር ሳይያያዝ የትምህርት ክፍያ መፈጸምን የመሳሰሉ ጉድለቶች በኦዲት ምርመራ መገኘታቸውን ገልጸዋል ።
በሰው ኃይል አስተዳደር በኩል ከታዩት ችግሮች መካከል ደግሞ ” ለፕሮጀክቱ ስራ የተቀጠሩ የጉልበት ሰራተኞችን የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት አመራሮች የግል ስራቸውን ማሰራትና የመስሪያ ቤቱን ተሽከርካሪዎች ለግል ጥቅም ማዋል ፣ከስልጣን ውክልና በላይና ማስታወቂያ ሳይወጣ ቅጥር ፈጽሞ መገኘት ፣በስራ ቦታ ሳይገኙ ደመወዝና የውሎ አበል መክፈል፣የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የተገለበጡ የመስሪያ ቤቱ ተሸከርካሪዎችን በመንግስት ስራ ላይ እንደነበሩ በማስመሰል ለጥገና የሚወጣውን ወጪ ከመንግስት ካዝና በማዘዝ የመንግስትን ሃብት ያለአግባብ ማባከን፣ከተፈቀደ በላይ ናፍጣ ወጪ በማድረግ ማባከን” የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
የቀረቡት ጉድለቶች በአብዛኛው በተለያዩ አጋጣሚዎች በመነጋገር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ቢነገርም ችግሩን ለመቅረፍ አለመቻሉን ባለሙያዋ ገልጸዋል።
ባለሙያዋ ይህንን ጉድለት የኦዲት ቡድኑ በሚያቀርብበት ጊዜ ስራውን በተመለከተ መስሪያ ቤቱን እስከሚያስተዳደረው ቦርድ ድረስ የደረሱ ጉዳዮች እንዳሉና በኮሚቴው አሰራር ያለመደሰት ሁኔታ የታየበት እና በኦዲት ቡድኑ ላይ ስጋት የፈጠረ ነገር እንዳለ ጠቁመው፤ የዋና መስሪያ ቤቱ የውስጥ ኦዲት ማስደረግ የሚፈልገው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ለስርዓቱና ለበላይ አመራሮች መልካም አመለካከት የሌላቸውን ሰዎች ለመምታት በተፈለገ ጊዜ ብቻ መሆኑን አጋልጠዋል፡፡
No comments:
Post a Comment