ኢሳት (ጥቅምት 17 ፣ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ተሸክሞ ያለው ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ጫናን አልፈጠረም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የአለም አቀፉ ሞኒተሪ ፈንድ (አይ ኤም ኤፍ) እና በርካታ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሃገሪቱ ተሸክማ ያለው ከፍተኛ ብድር ኢኮኖሚውን እየጎዳው እንደሚገኝ በመግለጽ ላይ ናቸው።
በሃገሪቱ የተከማቸ ብድር መጠን ከኢትዮጵያ አጠቃላይ አመታዊ ምርት 50 በመቶውን እንደሚሸፍንና ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን IMF በቅርቡ በቅቡ ባወጣው ሪፖርት መግለጹ ይታወሳል።
ይኸው የብድር መጠንም በውጭ ምንዛሪ ክምችት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የገንዘብ ተቋሙ ገልጸዋል።
ይሁንና በሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በፓርላማ ንግገርን ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሃገሪቱ ተሸክማ ያለው የብድር መጠን ወደ እዳ ጫና የሚከት አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።
የሃገሪቱ አጠቃላይ የብድር መጠን ከመግልጽ የተቆጠቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የብድር ምጣኔ ላይ የምትገኝ እንዳልሆን ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።
የአለም አቀፉ ሞኒተሪ ፈንድ (IMF) በበኩሉ የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ግማሽ ያህሉን በመሸፈኑ ጤናማ አለመሆኑን በመግለጽ መንግስት በቀጣይ በሚበደራቸው ገንዘቦች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።
የሃገሪቱ የወጪ ንግድ ማሽቆልቆል እና መንግስት በብቸኝነት የህዝብ ሃብትን ለሰፋፊ የልማት ፕሮጄክቶች ማዋሉ በኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎም ለአስቸኳይ መሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦችና መድሃኒቶች ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ እንዲሰጥ ተደርጎ የሚገኝ ሲሆን በርካታ አስመጪ ነጋዴዎች የንግድ እንቅስቃሴያቸው ተስተጓጉሎ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment