መስከረም ፳፭ (ኅያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመስተዳድሩ 10 ክፍለ ከተሞችና 116 ወረዳዎች የሚገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎች የሹም ሽር እና የሹመት ቦታ ለውጥ መረጃዎች የታወቁ ሲሆን፣ የማዕከል መ/ቤት ቢሮዎችና ሹም ሽር ድልደላ በዚህ ሳምንት የሚጠናቀቅ ሆኖ፣ በወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች አጠቃላይ ቁጥራቸው ከ800 የማያንሱ አመራሮች በሙስና፣ከድርጅቱ ጋር ባላቸው ተቃርኖ፣ በአመራር ብቃት ማነስ እንዲሁም በትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን በሚል ዝርዝር የግምገማ ሂደት እንዲነሱ ተደርጓል፡፡
ብዛት ያላቸው ካድሬዎች በተለይ በወረዳ ደረጃ የሚነሱት አመራሮች አኩርፈው ከድርጅቱ መስመር ውጪ እንዳይሆኑ በሚል ስጋት የከተማ አስተዳደሩ ድርጅት ጽ/ቤት ከድርጅት አመራርነታቸው የተባረሩ እና የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ አመራሮች በልዩ ትኩረት ድጋፍ ተደርጎላቸው በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው እንዲሰሩና በህይወታቸው ከህዝቡ የተሻለ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ሆነው እንዲኖሩ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው የሚል አቅጣጫ ተነድፏል፡፡
መስተዳድሩ እስከ 400 የሚሆኑ በሙስና የተዘፈቁ አመራርና ሲቪል ሰራተኞችን በህግ ተጠያቂ አደርጋለሁ ብሎ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑ ጥቂት አካላት በህግ አግባብ እንዲጠየቁ የክስ ሂደት እንዲጀመር ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ይሄ ተግባር ግን ወደ በላይ አመራሩ አካባቢ እንማይዘልቅ ከወዲሁ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ጉዳዩን የሚከታተሉ የከተማው የተለያዩ ህ/ብ ክፍሎች ይገልጻሉ።
ድርጅቱ ለይስሙላ ሙሰኛ አመራሮች ይጠየቃሉ ከሚል የመድረክ ፉከራ የዘለለ ርምጃ መውሰድ እንደማይፈልግ ከወዲሁ ያስታውቃል የሚል ቅሬታዎች በስፋት እየቀረቡ ነው። ኢህአዴግ ከጅምሩ ሙስንና የስርዓቱ ዋና መገለጫ አድርጎት ሳለ፣ የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጌ እየሰራሁ ነው በሚል ጥቂት የገቢዎች አመራሮችን አስሮ ተጠያቂ ማድረግ ጀምረናል ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል በሚል በየመድረኩ እያነሳ ፕሮፓጋንዳ ከመንዛት የተለየ ርምጃ ሲወስድ አለመታየቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment