ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአለም የምግብ ድርጅት በእንግሊዝኛው ( FAO) ተወካዮች በዚህ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝን አንድ የመጠለያ ካምፕ ከጎበኙ በሁዋላ ባወጡት መግለጫ፣ በአንዳንድ ወረዳዎች 95 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በረሃቡ ምክንያት አካባቢውን ለቆ ተሰዷል።
እጅግ በርካታ የቤት እንስሳት መሞታቸውን ይፋ ያደረገው ድርጅቱ፣ አሁንም ከፍተኛ የምግብ እጥረት በማጋጠሙ በተለይ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዱ ነው። በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙት 1 ሺ 400 ቤተሰቦች ባለፈው ግንቦት እና ሰኔ ወር መምጣታቸውን የገለጸው የምግብ ድርጅቱ፣ አብዛኞቹ እንስሶሳቸው የሞቱባቸው ከመጋቢት ወር ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።
ሱለይማን ገሌ የተባለው አርብቶ አደር ከድርቁ በፊት 500 በጎችና 60 ላሞች የነበሩት ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰአት የቀሩት 13 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 4 ላሞች ብቻ ነው። ማርያም የተባለች አርብቶአደርም እንዲሁ 100 በጎችና ፍየሎች የነበሯት ቢሆንም ሁሉም አልቀው ወደ መጠለያ ጣቢያ ለመምጣት ተገዳለች። ብዙዎቹ ተረጅዎች ለቀሩት እንስሶች የምግብና የውሃ አቅርቦት እንዲሟላላቸው ድርጅቱን ጠይቀዋል። እስካሁን የሚቀርበው ምግብ 10 በመቶ የሚሆኑትን ብቻ የሚሸፍንና ከ18 ቀን ለማይበለጥ ጊዜ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment