Monday, October 5, 2015

የአዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሰራተኞች በግዳጅ ስልጠና እየወሰድን ነው አሉ

መስከረም ፳፬ (ኅያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሰራተኞች ላይ ከኢሕአዴግ መንግስት የሚሰነዘረው የፖለቲካ ጠልቃ ገብነትና አፈና ከመቼውም ጊዜ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በምሬት ተናግረዋል።

የኢሕአዴግ መንግስት “ስልጠና’ በሚል ስም በአገር-አቀፍ ደረጃ ካዘጋጃቸው ስብሰባዎች አንዱ በሆነው ሰብሰባ ጠቅላላውን የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች ከሰኞ መስከረም 10 እስከ 16 2008 ዓ/ም አዳራሽ ውስጥ ሰብስቦ አሰልቺ የሆነ የፖለቲካ ቅስቀሳ ሲያደርግ መሰንበቱን መምህራኑ ተናግረዋል።
ይህ “2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” በተሰኘው ሀሳብ ዙሪያ “ስልጠና “ ተብሎ የተዘጋጀ ስብሰባ አንድም ሰው በማናቸውም ምክንያት መቅረት የማይቻል ጥብቅ ጉባዔ መሆኑ በቅድሚያ በማሰታወቂያ ና በየክፍሉ ሀላፊዎች በኩል መነገሩን የሚናገሩት መምህራን፣ በቀን አራት ጊዜ የመቆጣጠሪያ ደብተሩ ላይ እንዲፈርሙ ተገደዋል።

አንድ ጊዜ ወደ አዳራሹ ውስጥ የገባ ሰው ከሻይ ዕረፍት ወይንም ከስብሰባው ማብቂያ በፊት ተመልሶ መውጣት ፈጽሞ የተከለከለበት እገታ ነበር የሚሉት መምህራን፣ በዚህ አስጨናቂ ድባብ በተወጠረ አዳራሽ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በግዳጅ ታግተው ከክልል ቢሮዎች በተላኩ የትምህርት፤ የፖለቲካ ዕውቀትም ሆነ የአሰተሳሰብ ብስለት የለላቸው ነገርግን በባዶነት እብሪት በተወጠሩ ጀማሪ ካድሬዎች የግዳጅ ትምህርት እንዲሰጣቸው መደረጉን መመህራን በምሬት ተናግረዋል።
“ስልጠናውን አሰቂኝ የሚያደረገው” ይላሉ መምህራን፣ “አሰልጣኝ “ ተብሎ ያለዕፍረት መድረክ ላይ በተቀመጡት ካድሬዎችና “ሰልጣኝ “ በተሰኙት ምሁራን መካከል ያለው የዕውቀትና ግንዛቤ ክፍተት ብቻ ሳይሆን በሚነሱት ጭብጦችም ጭምር ነው።
አንዱ የመወያያ ርዕስ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ቢሆንም፣ ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው ጉዳዩ የኢሕአዴግ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ነው የሚሉት መምህራን ፣ ከ20 ዓመት በላይ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ህዝብ ሲንጫጫ ጆሮን የነፈገና አልፎ ተርፎም ሲከላከል የኖረ መንግሰት በአንዴ ተገልብጦ ለጥራት ተቆርቋሪ ሆኖ መቅረቡ ጉዳዪን ፍጹም ሸፍጥ ያደርገዋል ሲሉ ያክላሉ።
ሌላው አስገራሚና አሳዛኝ ጉዳይ በዩኒቨርሲቲው ሆነ በክልል አመራርነት ስም “አሰልጣኝ” ነን ብለው የመጡ ካድሬዎች ዓይንአውጣነት ነው፡፡
ጉዳዩን በዋናነት የሚያወያዩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ 2ኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት በቅርቡ ሲሆን የተማሩትም አዋሳ ዪኒቨርሲቲ ስር በክልሉ መንግሰት ቀጥተኛ ጥያቄ ለክልሉ ከፍተኛ ካድሬዎች አቅም ግንባታ በትዕዛዝ በተከፈተ ማሰተርስ ፕሮግራም ሆኖ ውጤትም በትዕዛዝ እየተሰጣቸው መሆኑን ያሰተማሯቸው መምህራን ተናግረዋል።
የግዳጅ “ሰልጠና“ ላይ ያለፈውን ሳምነት ያሳለፉት መምህራን በዚህ ሳምንት በተራቸው በግዳጅ ተማሪዎቻቸው ፊት እየቀረቡ “የሰለጠኑትን“ ጭብጥ “በሰለጠኑት“ መንገድ ለተማሪዎች እንዲያሰተላፉ ታዝዘዋል፡፡
ጭብጡ ሙሉ በሙሉ ልማታዊ ዴሞክራሲ በሚል ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ኀልዮትና ፕሮፓጋንዳ የሆነውን ይህን “ሰልጠና“ የድርጅቱ አባል ያልሆኑ መምህራን፤ ተማሪው ፊት ቁመው እንዲያነቡ አሊያም ስራቸውን እንዲለቁ በግልጽ ተነግሯቸዋል።
እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በመምህራን “ሰልጠና“ ያልተሳተፉና በስልጠናውም ማብቂያ ላይ ተገምግመው “ሂስ ያላወረዱ“ መምህራን እንዲሁ የማሰተማር ሥራቸውን መጀመር እንደሌለባቸው ካድሬዎቹ በይፋ ተናግረዋል፡፡
በሁኔታው የተደናገጡና ወትሮውም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ እየተሰቃዩ ያሉት መምህራን በከፍተኛ ግራ መጋባትና ምሬት ተውጠዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የማያውቁትንና የፖለቲካ እምነታቸው ያልሆነውን የ “ሰልጠና“ ሰነድ ይዘው ተማሪዎች ፊት ቀርበው ቃል በቃል እያነበቡላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ግን የሚመጣዉን ለመጋፈጥ ራሳቸውን ከዲደቱ አገልለው በመጠባባቅ ላይ ይገኛሉ።
በተማሪዎችም በኩልም “ሰልጠናው“ ፍጹም ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን ተማሪ ከግቢ እንዳይወጣ በር ላይ ከሚደረግ ክልከላ በተጨማሪ በየመኝታ ክፍሉ ጥበቃ ሰራተኞች ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ በግዳጅ “ሰልጠናው“ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ውስጥ እንዲቀመጡ እያደረጓቸው እስከ እሁድ መስከረም 23 ቀን ድረስ መቀጠሉን መምህራን ገልጸዋል።
ሁኔታው የመምህራንና ተማሪዎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በጠራራ ፀሐይ የናደ ከመሆኑም በላይ የመምህራንን ክብርና ሞራል ያላሸቀ፤ የሥራ ዋስትናውን ያጨለመ እና ሁለት ሳምንት ወርቃማ የትምህርት ጊዜን በፌዝና ሸፍጥ እንዲቃጠል ያደረገ የንትርክ መድረክ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል ሲሉ መምህራን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment