መስከረም ፳፬ (ኅያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች “መልካም ስም ከመቃብር በላይ ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል” በሚል ርዕስ ባወጡት መግለጫ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ፤ ብሎም ለአዲሱ የፕሬስ ትውልድ ፈር ቀዳጅ የነበረው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ከዚህ አለም በሞት መለየቱ ለብዙዎች የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች እና ቤተሰቦች መሪር ሃዘን ነው ብለዋል።
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በአንደበቱ እውነትን የመሰከረ፤ በሰላ ብዕሩ ሃቅን የፈነጠቀ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ምሳሌ ሆኖ ያለፈ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉም አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
“የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ፤ የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ታሪክ ይወሳል። የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ገድል ሲታወስ ደግሞ፤ የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ መልካም ስም እንደ ፈርጥ ያንጸባርቃል። ” የሚለው መግለጫው፣ በውጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌን እንደታላቅ ወንድም፤ እንደሙያ አጋር እና እንደ ጥሩ ምሳሌ እያነሱ መልካም ተጋድሎውን ያስታውሳሉ። መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላልና የጋሽ ሙሉጌታ ስራ እና ስም ለዘለአለም በክብር ይታወሳሉ።” ብሎአል።
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ስለራሱ ታሪክ ባይጽፍም፣ በተለያዩ አገራዊና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጽሁፎችን አበርክቷል። በተለይም በኢሳት ላይ ቀርቦ የሚሰጣቸው ትንተናዎች፣ ብዙዎች ከፍተኛ የሆነ ትምህርት እንዳገኙበት ለኢሳት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ በገዢው ፓርቲ ተጽእኖ እንዲፈርስ በተደረገው ጦቢያ መጽሄት ተከታታይ ጽሁፎችን በማቅረብ በርካታ አንባቢዎችን አፍርቷል።ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌን የተመለከቱ ዝግጅቶችን በተከታታይ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
No comments:
Post a Comment