ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች መንደር
መብራቱን አጥፍቼዉ አልጋዬ ላይ የወጣሁት በግዜ ነዉ። አለወትሮዬ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኔ አልዞር ብሎኝ ከጨለማዉ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠናል። የነፋስ ሸዉታ እንኳን የማይሰማበት ደረቅ ሌሊት ነዉ። ጨላማዉ አይን ይበሳል። እቤቱ ዉስጥ ያለዉ ሰዉ ሁሉ ተኝቷል። ቀኑን በሠላም ላዋለኝ አምላክ ምስጋና ሰጥቼ ሌሊቱንም አደራ ብዬዉ ፀሎቴን ጨረስኩ። ያ ምቀኛ እንቅልፍ ግን አሁንም እንደከዳኝ ነዉ። ትንሿ አልጋዬ ላይ ግራ ቀኝ እያልኩ ተገለባበጥኩ። እንቅልፍ ተጎትቶ የሚመጣ ይመስል አሁንም አሁንም ላይ ታች እያልኩ አልጋዉ ላይ እራሴን ጎተትኩት . . . እንኳን እንቅልፍ ሊወስደኝ ጭራሽ አይኖቼ መርገብገባቸዉን ያቆሙ ይመስል ቀጥ ብለዉ ቀሩ። ከተጋደምኩበት ብድግ ብዬ መብራቱን አበራሁና ለመንገድ ከያዝኳቸዉ ሁለት መጻህፍት አንዱን አዉጥቼ ማንበብ ጀመርኩ። እኔ ላንብበዉ ወይ መጽሀፉ ያንብበኝ አላዉቅም። ጧት ስነሳ ግን “The Architecture of Democracy” የሚል መጽሐፍ ደረቴ ላይ ተለጥፎ ነበር። ሰዐቴን ሳየዉ ከሌሊቱ ስምንት ሰዐት ተኩል ይላል። ከአልጋዬ ላይ ዘልዬ ወረድኩና ሰዉነቴን ታጥቤ ልብሴን ከለበስኩ በኋላ መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ “I’m ready” አልኩ። የመኪናችን መብራት ጨለማዉን እየገላለጠዉ የአስመራ ከረንን መንገድ ተያያዝነዉ። መኪናዉ ዉስጥ ከገባሁ በኋላ እንደገና አፌን የከፈትኩት ባሬንቱ ደርሰን ቁርስ ሳዝ ነዉ። ባሬንቱ በግዜ መድረሳችን ደስ ቢለኝም የቀረን መንገድ ርዝመት ታየኝና ቁርስ መብላቴን ትቼ . . . በሰዐት ይህን ያክል ብንጓዝ እያልኩ ዋናዉ ጉዳያችን ቦታ የምንደርስበትን ሰዐት ማስላት ጀመርኩ። የስሌቱ ዉጤት ከሦስት ሰዐት ሲበልጥብኝ ተናደድኩ። ቀሪዉ መንገድ ገና ሳልጀምረዉ ሰለቸኝ። በተፈጥሮዬ መንገድና መኃላ ሲረዝም አልወድም።