ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2008)
በቅርቡ በኢትዮጵያ ረቅቆ ለምክር ቤት የቀረበው የኢንተርኔት አጠቃቀም ህግ በአገሪቱ ያሉትን የመንግስት ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የድረ-ገጽ ተጠቃሚዎችን ድምፅ ለማፈን ሆን ተብሎ የታቀደ ህግ እንደሆነ በኬንያ የሚታተመው ኦኬ አፍሪካ የተባለው ጋዜጣ ዘገበ። በኢትዮጵያ የቀረበው አዲስ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ተብሎ የሚጠራው ረቂቅ ህግ በብዛት የሚሰራጩ የጹሁፍ መልዕክቶችን ተቀብሎ ማሰራጨት በወንጀል እንደሚያቀጣ ያትታል።
በኬንያ የሚታተመውና ኦኬ አፍሪካ የተባለው ጋዜጣ “የቡና አገር እንጂ በቅርቡ የኢሜይል አገር የማትሆነው ኢትዮጵያ” የጹሁፍ መልዕክቶችን በድረ-ገጽ ወይም በስልክ በብዛት የሚያሰራጩ ዜጎችን እስከ 5 አመት ድረስ በሚደርስ እስራት እንደምትቀጣ ዘግቧል።
የ”ኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ” በመባል የሚታወቀው ይኸው ህግ፣ የጹሁፍ መልዕክቶችን በማስታወቂያ መልክ፣ እንዲሁም ፎቶና ቪዲዮ በብዛት የሚያሰራጩትን ለመቆጣጠር እንደወጣ በመግለጽ፣ አንድ ሰው ሆን ብሎ ሌላ ሰውን ወይም ቤተሰቡን ቪዲዮ በመስራት፣ ድምፁን ወይም ምስሉን በማሰራጨት ማስፈራራት፣ አደጋ ማድረስ፣ ወይም ስም ማጥፋት እንደወንጀል ተቆጥሮ እስከ ሶስት አመት በሚደርስ እስር እንደሚያስቀጣ፣ እና ጉዳዩ ከባድ ከሆነ እስከ 5 አመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስፈርድ ኦኬ አፍሪካ በዘገባው አስፍሯል።
በተጨማሪም የወሲብ ምስሎችን ማሰራጨት፣ ስርቆትን ማበረታታትና እና ኮምፒውተር መጥለፍ በተለምዶ ወንጀል ቢሆኑንም፣ በዚህ ህግ የተካተተው “ተቃውሞ መጥራት” ወይም “ህዝብን ማተራመስ” የሚለው ሃረግ ግን አስገራሚ እንደሆነ ጋዜጣ የረቂቁን ክፍል በማጣቀስ ገልጿል።
ኦኬ አፍሪካ እንደዘገበው፣ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ በህግ ደረጃ መውጣቱ መንግስት ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንና፣ በኢንተርኔት የሚጠቀሙትን የመንግስት ፖሊሲ ተቺዎችን ሁሉ ገጽታዬን ያበላሹብኛ ብሎ ስለሚሰጋ ህጉን ለማስፈራሪያነት እንደሚጠቀምበት አክሎ ገልጿል።
በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ወንጀል ህግ የወጣው፣ መላው የኦሮሚያ ክልል በተቃውሞ ስትናጥ መቆየቷን ተከትሎ እንደሆነ ጋዜጣው ገልጾ፣ በተቃውሞው ወቅት የድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች በመንግስት ሃይሎች የተገደሉትን ዜጎች በመልዕክት መላላኪያ በሆኑ እንደትዊተር፣ ዋትስአፕ፣ እና ፌስቡክ በመሳሰሉ በመቀባበላቸውና ወንጀሉን በማጋለጣቸው እንደሆነ አመልክቷል።
ጋዜጣው በታንዛኒያ ውስጥም የመንግስት ሰራተኞች የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን በስራ ሰዓት እንዳይጠቀሙ በመከልከል በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚደረገው “ሃሜት” ከስራ ያስባርራል ሲል ባለፈው መጋቢት የወጣውን ህይ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። በተመሳሳይ መልኩም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ማገድ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በዋናነት የሚስተዋል እንደሆነ ገልጾ፣ ዜጎች በዚምባቡዌ፣ በጋምቢያ፣ በኡጋንዳና በኮንጎ ብራዛቢል የድምፅ መጭበርበር፣ ማስፈራራት፣ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እስርን በተመለከተ ተቃውሞኣቸውን እንዳያሰሙ “የጸጥታ ችግር ሊኖር ይችላል” በሚል ሰበብ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደሚዘጉ ጋዜጣው ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment