ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)
በአሁኑ ሰዓት በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ አራት የተማሪ መኖሪያ ህንጻዎች በእሳት እየነደዱ መሆናቸውን ተማሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
የእሳቱ መነሻ ምን እንደሆነ እንዳልታወቀ የገልጹት ምንጮች፣ 4ቱ ህንጻዎች ከ400 በላይ ተማሪዎች ይኖሩባቸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የተቃጠሉ ደመራ የሚባሉት ህንጻዎች እንደሆነ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ የተማሪዎች ንብረቶች ከመውደማቸው ውጭ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ ለማወቅ አልተቻለም።
ተማሪዎች እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉ ሲሆን፣ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ዘግይቶ በአካባቢው እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል።
የመንግስት ወታደሮች፣ እና ልዩ ጦር ሃይል አባላት በግቢው ውስጥ መታየታቸውንም እነዚሁ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደረግ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ ትምህርት ተቋርጦ ቆይቷል። ሆኖም ከሴሜስተር ዕረፍት በኋላ ትምህርት በተወሰነ መልኩ ተጀሞሮ እንደነበር የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ይገልጻሉ። በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተቃውሞውን ተከትሎ በተለያየ ጊዜ በቁጥር ሊታወቁ ያልቻሉ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲው መባረራቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment