ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ አንድነት የመጠበቅና የታሪክ ህፀፆችን ማረም ከአዲሱ ዘመንት ዲሞራቶች ይጠበቃል ሲል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ገለጸ። ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ የዘንድሮ ግንቦት 20” በሚል ርዕስ ሰሞኑን ከወህኒ ቤት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው ፅሁፍ ኢህአዴግ ወደስልጣን የመጣበትን 25ኛ አመት በማስመልከት ያለፉትን 50 አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመገምገም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።
በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ውስጥ የነበረው የሃይል አሰላለፍ እንዲሁም በህብረ-ብሄርና በብሄር ፓርቲዎች መካክል የነበረውን ልዩነት በመዘርዘር ለኢትዮጵያ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅ ጥሪ አቅርቧል።
“ተማሪዎች እንቅስቃሴያቸውን ከጀመሩ ከ55 ዓመታት በኋላም የዮሃንስና የምኒሊክ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ የፈጠረው ሽኩቻ የኢህአዴግ ቅኝት ጸረ-ዲሞክራሲ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት ግብዓቶች መካከል አንዱ ሆኖ ይገኛል ያለው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሲያጠቃልልም “የታሪክ ጣጣ የኦሮሞና የሶማሌ ብሄርተኞችን ነፍስ ዕረፍት እየነሳ ነው፥ የታሪክ ህፀጾች የማይቀበሉ ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ሃይሎችም አሉ፥ ይህ ሁሉ ተደማምሮ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፣ መፍትሄውም ከአዲሱ ዘመን ዲሞክራቶች ይጠበቃል” በማለት ለሃገሪቱ ችግር ዕውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚጠበቅ ጥሪ አቅርቧል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከመስከረም ወር 2004 ጀምሮ በአሸባሪነት ተከሶ በወህኒ ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ የ18 ዓመታት እስር እንደተፈረደበት ይታወቃል። ክሱም ሆነ ፍርዱ እውነትም ሆነ ህጋዊ መሰረት እንደሌለው ለማመልከት ወይንም በፖለቲካ አመለካከቱ መታሰሩን ለማስረዳት በጽሁፉ ግርጌ “የህሊና እስረኞች” ሲል አስፍሯል።
No comments:
Post a Comment