ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2008)
ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሃገራት የመገናኛ ብዙህን ነጻነት እያሽቆለቆለ መምጣቱን በጉዳዩ ዙሪያ ጥናትን ያደረገ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ረቡዕ ይፋ አደረገ።
መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገውና የ2015 ሪፖርቱን ለህዝብ ይፋ ያደረገው ፍሪደም ሃውስ (Freedom House) እኤአ አቆጣጠር በ2015 የአለም የመገናኛ ብዙሃን ባለፉት 12 አመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አሽቆልቁሎ መገኘቱን አስታውቋል።
ከአፍሪካ ቡሩንዲ፣ በመገናኛ ብዙሃን ላይ በምትወስደው የከፋ እርምጃ ግንባር ቀደም ተደርጋ የተቀመጠች ሲሆን በቅርቡ የውጭ መገናኛ ተቋማት ወደሃገሩ እንዲገቡ የፈቀደችው ጎረቤት ኤርትራም ጋዜጠኞችን በማሰር የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ተግባራዊ እንዳላደረገች ፍሪደም ሃውስ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
ተደጋጋሚ ትችት የሚቀርብበት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በመንፈግ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን አፍኖ መቀጠሉን ድርጅቱ ገልጿል።
ሃገሪቱ የረቀቁ የኢንተርኔት የስለላ መሳሪያዎችን በመጠቀም ስልኮችን በመጥለፍና በተጓዳኝ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ላይ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በተለየ መልኩ ተሰማርታ መገኘቷን ደግሞ በሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ተመራማሪ የሆኑንት ፊሊክስ ሆርን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የረቀቁ የስለላ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የበርካታ ግለሰቦችን ስልኮችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መገልገያ ቁሶችን በመጥለፍ ሰዎችን ለእስር ዳርጎ መቆየቱንም ሃላፊው ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
በአፍሪካ ግንባር ቀደም የመገናኛ ብዙሃን ጠላት ተደርገው በሚታወቁት ሃገራት ላይ ጠንካራ እርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት ሌሎች ሃገራት ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸውንም ፍሪደም ሃውስ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
በመገናኛ ብዙሃን ነጻነታቸው ይታወቁ የነበሩት ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ጠንካራ ዕርምጃ መውሰድ እንደጀመሩና ድርጊቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጀኒፈር ዱንሃም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
በአለማችን ካሉ ወደ ሰባት ቢሊዮን ህዝብ መካክልም 13 በመቶ ብቻ የሚሆነው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ያገኘ ሲሆን 41 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በከፊል የመገናኛ ነጻነት እንዳለው ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
ከአለም ህዝብ መካከልም 46 በመቶ የሚሆኑት የመገናኛ ነጻነት የሌላቸው እንደሆኑ ያስታወቀው ፍሪደም ሃውስ ፥ ባንግላዴሽ፣ ቱርክ፣ ቡሩንዲ፣ ፈረንሳይ፣ ሰርቢያ፣ የመን፣ ግብፅ፣ ማክዶኒያና፣ ዜምባብዌ የነበራቸው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት በ2015 እጅጉን አሽቆልቁሎ ተገኝቷል።
በደረጃ ከተቀመጡ 50 የአፍሪካ ሃገራት መካከልም ኢትዮጵያ የከፋ ሪከርድን በማስመዝገብ በ46ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
No comments:
Post a Comment