ቀን፡ ሚያዝያ 10/2008 ዓ/ም
እኛ የወልቃይት ጠገዴ የጎንደር አማራ ህዝብ የወያኔ ሴራዋን አውቀን ብንታገስም እንኳ በምታደርስብን ስቃይ ወደ ግጭት እንድንገባ በማድረግ ህዝባችንን ለመጨረስ ዝግጅት እያደረገች ነው!!!
በዚህ ሳምንት በወልቃይት ጠገዴ በዳንሻ ከተማ የሚገኙ ሁለት የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች “የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጎንደሬ አማራ ነው” ብላችሗል ተብለው ከትምህርት ገበታቸው ተባረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትምህርት ቤቱ የሚያስተምር አንድ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ መምህር ገ/ፃድቃን ከተባለ
ትግሬ የኬምስትሪ መምህር ጋር “ወልቃይት ጠገዴ አማራ ነው” ብሎ ስለ ተከራከረው ብቻ ከትግራይ አስተዳደሩ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት ይገኛል።
ሌላው አስገራሚ የሆነው ክስተት ደግሞ በትላንት እለት በቃብቲያ በጠቅላላው ደግሞ በዚህ ሳምንት በአዲረመጥ የወልቃይት ህዝብን የክልል ሃላፊዎች ስብሰባ በማካሄድ “መሬት እንስጣችሁ ፤ ተሰብሰቡ”
ሲሏቸው “ይህ የቆማችሁበት ወልቃይት የተባለ መሬትና ህዝብ እናንተ እንደምትሉት የእናንተ የትግራይ ሳይሆን የጎንደር ስለሆነ መሬቱ የኛ የራሳችን የጎንደሬዎቹ ሆኖ ሳለ ከየት ያገኛቹሁት
መሬት ነው የምትሠጡን?” ብለው በጥያቄ ካፋጠጧቸው ብሗላ “ይልቁንስ ልትረዱት የሚገባችሁ እውነት የእናንተ መሬት ከተከዜ ማዶ ያለውን ትግራይ የተባለው መሬት ስለሆነ ተከዜ ማዶ ሂዳችሁ አስተዳድሩ” በማለት ጀግናው ህዝብ በጀግንነት አቋሙን አሳውቋቸዋል።
ይሔን ሃፍረት የተከናነበው የትግራይ መንግስት በብስጭት በዛሬው ቀን በዳንሻ ከተማ ልዩ የሆነ የጅንጀና ስብሰባ ሲያካሂድ ዉሏል። ኒዮሊባራሊዝም የሚባል ፖሊቲካ ለህዝቡ ሲለፈለፍ ውሏል። ህዝቡን “እኛ ትግሬ ነን፤ ኮሚቴው እኛን አይወክልም” ብላችሁ ሰላማዊ ሰልፍ ውጡ። ይህን ካደረጋችሁ የልዩ ልዩ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ትሆናላችሁ በሰላምም ትኖራላችሁ እያሉ በጥብቅ ሲያሳስቡ ውለዋል።
ወያኔ ለድሮ ሰፋሪ ታጋዮቹም ሆነ ለአዲሶቹ ሰፋሪዎቹ ትግሬዎች ቅስቀሳ እያካሄደ መሳሪያ እያደላቸው ነው። የማይታወቁ አዳዲስ ትግሬዎች በየቀኑ በህዝባችን መሃል እየተገኙ ፍርሃትና ዛቻ እያደረሱብን ነው። ሌላው ከዚህ ጋር የተያያዘ በዚህ ሳምንት ያየነው አዲስ ክስተት ደግሞ ከአሁን በፊት አይተናቸው የማናቅ ብዙ አዳዲስ ፖሊሶችም ህዝባችንን እያንገራገሩ ኑሯችንን ምስቅልቅል በማድረግ አገራችንን ጥለን እንድንሰደድ በአይነቱ ልዩ ልዩ የሆነ ጫና እያደረሱብን ነው። ሳንወድ በግድ ህልውናችንን ለማስቀጠል ስንል ወደማይቀረው ጦርነት እንድንገባ በጣም እየገፋፉን ስለሆነ የፍትህ ያለህ እንላለን!!!
እኛ እንደ ህዝብ ወደ ጦርነት መግባት አንፈልግም ጉዳይችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ህገ- መንግስታችን እንዲፈታልን ነው የምንጠይቀው። የትግራይ መንግስት ግን በህዝባችን ግጭት የተፈጠረ በማስመሰል ወይንም በሚደርስብን ልዩ ልዩ ስቃይ ተነስተን ወደ ግጭት እንድናመራ በማድረግ ሆን ብሎ በህዝባችን ላይ ጦርነት በመክፈት ሊጨርሰን እየተዘጋጀ ነው ያለው። የትግራይ መንግስት እያንዳንዱ በወልቃይት ጠገዴ የሚገኙትን ትግሬዎች የሞት ድግስ በመደገስ “ተጋዳላይ ትግራይን” የሚለውን ዘፈን ከፍቶ በማስጨፈርና በማስታጠቅ ሊያጫርሰን ተዘጋጅቷል። እኛ እንደሆን ወደሗላ አንልም!!! ማንነታችንን ማስከበር ህገ-መንግስታዊ መብታችን ስለሆነ ማንኛውም አይነት መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ይህን ስንል ግን የሚዳኘን መንግስትና ህዝብ አለን ብለን ስለምናምን ወደ ጦርነት መግባት አንፍልግም እንላለን እንጂ ፍርሃት እንዳልሆነ ሊረዱት ይገባል። ይገርማችሗል የሚነፍሰው ነፋስ ሁሉ ባሩድ ባሩድ ይሸታል፤ አዝማሚያው ሁሉ ደም ወደ መፋሰስ እየመራው ነው!!! ወንዶቻችንም ይሁን ሴቶቻችን በሰላም ውለው መመለስ እየቻሉ አይደለም፤ ይህ ነገር በቃላት ከምገልጥላችሁ በላይ ሆኖ አሳራችንን እየበላን ነው። እያንዳንዷ ሴኮንድ የአንድ ቀን ያህል እየረዘመብን ስለአማራ ማንነታችን ስንል በልዩ ልዩ የስቃይ ወላፍን እየተገረፍን ነው ያለነው።
ከስብሰባ ውጭ እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ “እናንተ ፈሪዎች ጀግንነታችሁ ታድያ የት አለ? ወልቃይት ጠገዴ ደፋር ነው ምናምንቴ የምትሉት አጉል ጉራ ነው! እንዲያውም አማራ በጉራ ነው የሚኖረው” በማለት እነርሱ የኛን አማራነት ቢያረጋግጡም ስድባቸውና ጫናቸው ግን ትዕግስታችንን በጣም እየተፈታተነን ነው። እንዲህ በማድረግ ሰላማዊ ጥያቄያችንን በማደፍረስ ወደ ግጭት እንዲያመራ መፈለጋቸውን አውቀን በትዕግስት የሚያደርሱብንን ግፍ ለመቋቃም ብንሞክርም በነውረኛ ውንብድናቸው በሰላም ወጥተን እንዳንገባ በማድረግ ለሰላም ስንል በቁም እስር እንገኛለንና የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሆይ የአማራ ማንነታችንንና ሰላማችን እንዲከበርልን እርዳታችሁ አይለየን። የትግራይ መንስግስትና ሰፋሪ ካድረዎቿ እያደረሱብን ያለውን ግፍና ሰቀቀን እንዲያቆሙ በፍጥነት አሳስቡልን!!!
በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ወገናችን የሆነውን የትግራይን ህዝብ ይወክላሉ በለን አናምንም፤ እምነታችን ይህ ሆኖ ሳለ ግን የትግራይ መንግስት ከአሁን በፊት የደረሰብንን ግፍ ይቅርታ እንደመጠየቅ በእኛ ህዝብና በትግራይ ህዝብ መካከል የትውልድ ደምነት ለመትከል ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ለትግራይ ህዝብ ማሳሰብ የምንፈልገው ጉዳይ ቢኖረን በክፉም በደጉም ለብዙ ሺ ዘመናት በፍቅር እንዳልኖርን ልጆቻችሁ እየፈፀሙብን ያለውን ግፍ እንዲያቆሙ ምከሩዋቸው አለያም በሰላማዊ ሰልፍ አስረዱዋቸው እንላለን።
ጦርነትን ለማወጅማ እኛው ነበር ማወጅ የነበረብን ነገር ግን እኛ እንደነርሱ እብዶች አይደለንም አርቆ አሳቢዎች ነን። ለውጭ ጠላት ቢሆንማ ኖሮ እንዴት ፈጣን ጀግኖች እንደሆን እነርሱም በደምብ
ያውቃሉ። እኛ ግን እጅግ በጣም ሰላም ወዳዶች ነን። ልጆቻችሁ ምንም ክፉ ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን እንደመሆናቸው መጠን ጦርነት በማወጅ ድል የእኛ ብትሆንም እንኳ እንደ ድል የማይቆጥር አስተዋይ ህሊና ስላለን ልጆቻችሁ ሴት አዛውንቱ ሳይቀር ጠብመንጃ ይዘው አፎሙዙ በእኛ ግምባር ላይ እያነጣጠሩ ጦርነታዊ ሰልፍ ቢያደርጉብንም እብደታቸውን በፍጥነት እስኪያቆሙ ይሔው በትዕግስት እንጠብቃለን። በእርግጥ ‘የግዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውምና’ የግዜ ባለቤት የሆነው ግፍን አጥብቆ የሚጠላ አምላክ ከእኛ ጋር እንደሆነ በሙሉ ልባችን እናምናለን። ወያኔና ካድሬዎቿ ማንነታቸውን ተነጥቀው አላዩትም እንጂ የማንነት መነጠቅ ማለት በዚህች ምድር ላይ የሞት ሞት መሆኑ ማን ባስረዳቸው? ሞትኮ ለተገፋና ለተከፋ ህዝብ ድልን እንደሚያቀዳጀው ገና አልተረዱትም። ነገር ግን የተገፋ ህዝብ ሲሞት ጠላቱን ድል እያደረገ ነው። በሞቱ የተገፋ ህዝብ ህያው ሲሆን ጠላት ግን ነገሩ ተገልብጦበት የሞት ሞት ሞት ነው የሚሞተው ከሁሉም በላይ ደግሞ አሟሟቱ የሞት ሞት ሞት የሆነ ሞት ነው።
እንደ ኢትዮጵያውያን ነገሩን ሰፋ አድርገን ስናየው በእኛ እምነት ወገንን ለመግደል በሚደረግ የእርስ በርስ ጦርነት በሁለቱም በኩል ኪሳራ ብቻ የሚያጭድ አካል እንጂ ድል አድራጊ አካል ሊኖር አይችልም የሚል ጽኑ ኢትዮጵያዊ አቋም አለን። ልንታገስ የመረጥነውም ከዚህ አስተሳሰብ አንጻር ነው እንጂ እኛ የወልቃይት አማራ ህዝብ በጦርነት ውስጥ ክር እንደምንበጥስ እያጣጣሉን ያሉት ወያኔና ካድሬዎቿ እንኳ በደምብ ያውቁናሉ። ወያኔዎች ጉዳዩ ወደ ሌላ የማይመለስ ግልፅ እርስ በርስ ጦርነት እየነዱት ነውና አሳፋሪ ሊሆን የሚችለው ድርጊት ከመከሰቱ በፊት አስቸኳይ መፍትሔ ትፈልጉለት ዘንድ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሆይ እነሆ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ጉዳያችንን በሰላምዊ መንገድ መፍታት የሚችል የህገ-መንግስት ሰነድ እያለን ለማንነት ሲባል በሰለጠነው አለም ለ21ኛው መ.ከ.ዘ የማይመጥን ዋጋ አገራችን በወንበዴዎቹ ክፉ አሰራርና መንፈስ ምክንያት ከመክፈል ትታደጓት ዘንድ አሁንም ጥሪያችንን ደግመን እናቀርባለን። ግዜ የሚሰጥበት ሁኔታ አይደልም ያለው!!!
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በልዩ ሁኔታ ደግሞ የአማራ ህዝብ አሁንም ቢሆን ከጎናችን እንድትቆሙና የወያኔ ግፍ “ይብቃ!” ትሉልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን። በመላው አለም ያላችሁ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዉን ሰቆቃችን ለአለም ህዝብ ታሰሙልን ዘንድ በፈጣሪ ስም እንማጸናለን!!!
መይሳው ካሳ ነኝ ከወልቃይት ጠገዴ፤ በጌምድር፤ጎንደር ሚያዝያ 10/2008 ዓ/ም
No comments:
Post a Comment