መጋቢት ፳፫( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በደባርቅ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ልዩልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደተናገሩት ውይይቱ በከተማዋ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲነጋገሩ መገደቡ፤ በዙሪያቸው የሚካሄዱ ጉዳዮችን ሰምተው እንዳልሰሙ እንዲሆኑ መጠየቁ ህገመንግስታዊ መብትን የጣሰ አካሄድ ነው በማለት ክልሉን አስተዳድረው አለሁ በሚለው ብአዴን ማፈራቸውን ገልጸዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ “እንዲያውም መነጋገር የነበረብን በወልቃይት ጉዳይ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ አሁን የሁላችን ጉዳይ ሆኗል፤ መድረኩ ቢከፈትና ስለወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ እኛም አስተያየት መስጠት ብንችል መልካም ነው ፡፡” በማለት ያደረባቸውን ቅሬታ በርካታ ተሰብሳቢዎች ቢናገሩም፣ መድረክ መሪዎች “አላስፈላጊ ርዕስና ምላሽም የሚሰጥ የአማራ ክልል ኃላፊ የለም፡፡” የሚል ምክንያት በመስጠት ጉዳዩ እንዳይነሳ አድርገዋል፡፡
አንድ ተሰብሳቢ ሃሳባቸውን ሲገልጹ “ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ብሎም አማራ፣ብሎም ጎንደሬ ነኝ፡፡” በማለት ጀምረው የተሰብሳቢውን ድጋፍ ካገኙ በኋላ “ኃሳባችን ሊገደብ አይገባውም ነበር፡፡ኢትዮጵያዊ ሆነን ስለኢትዮጵያ እንዳናወራ ፣አማራ ሆነን ስለአማራነታችን እንዳናወራ እንደ መድረክ ህግ ሆኖ መቅረቡ ሳናምንበት የተቀበል ነው ፡፡” በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
አንድ ተሰብሳቢ ሃሳባቸውን ሲገልጹ “ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ብሎም አማራ፣ብሎም ጎንደሬ ነኝ፡፡” በማለት ጀምረው የተሰብሳቢውን ድጋፍ ካገኙ በኋላ “ኃሳባችን ሊገደብ አይገባውም ነበር፡፡ኢትዮጵያዊ ሆነን ስለኢትዮጵያ እንዳናወራ ፣አማራ ሆነን ስለአማራነታችን እንዳናወራ እንደ መድረክ ህግ ሆኖ መቅረቡ ሳናምንበት የተቀበል ነው ፡፡” በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ሌላው ጠንከር ያለ ኃሳብ ያቀረቡት ተሰብሳቢ ጉዳያቸውን ሲጀምሩ “አማራ ፣በፍትህ ከሄደች በቅሎዬ ያለ ፍርድ የሄደች ድምቡሎዬ የሚል አባባል አለው፡፡” በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ተነስተው፤ በፍርድና በፍትህ የሚገኘውን ልዕልና ከፍ የሚያደርግ ብሂል መሆኑን በመግለጽ በወልቃይት አማራ ላይ እየተካሄደ ያለው የማንነት ጥያቄ ፍትህ ማጣት በመድረኩ እንዳይነሳ መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክለውም “ሁሉም እዚህ የተሰበሰበው በከተማዋ ችግር ብቻ ለመወያየት አይደለም ፡፡የወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ እኛንም ያሳስበናል፡፡ የክልሉ መንግስት ብአዴን እንደ ድርጅት “ወልቃይት ለብአዴን ምኑ ነው?” ሊል አይገባም፡፡ ወልቃይት ላይ እየደረሰ ላለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ የአማራን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው መንግስት ጣልቃ ሊገባ ይገባል፡፡” በማለት ህብረተሰቡ በወልቃይት አካባቢ ላሉ ወገኖቹ ያለውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡
“በእውነት እያፈርንባችሁ ነው!” የሚሉት አስተያየት ሰጪ “በአማራ ወገኖቻችን ላይ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚደረገው ሰቆቃና ግድያ የአማራን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው ብአዴን ስለ አማራው ህዝብ ለምን አይጮህም? የአማራን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር ለምን አይንቀሳቀስም? የህዝቡን አንድነት ለመጠበቅ ለምን ጥረት አያደርግም?” በማለት በአካበቢው በአማራ ወገኖች ላይ የሚካሄዱ ጫናዎች ላይ ህብረተሰቡ እንዳይሳተፍ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
“በአካባቢው በሚደረጉ የአማራ ማንነት ጥያቄ ያገባናል!!” የሚሉት ተናጋሪው፣ የብአዴን አባል የሆኑ የአካባቢው ባለስልጣናትም በዙሪያቸው ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ባይተዋር መሆናቸው አግባብ አለመሆኑን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
“በአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚካሄደው ነገር ሁሉ እኛንም ያመናል! በወልቃይቶች ላይ የሚደረግ ኢሰብአዊ ድርጊትና የወንድሞቻችን ሞት ያንገበግበናል! የማይሰማን አይምሰላችሁ!” በማለት ብአዴን አማራን የሚወክል ከሆነ ነገሬ ብሎ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ በቁጭት ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል በወልቃይት ጉዳይ የአማራን ክልልም ሆነ የፌደራል መንግስትን አይመለከተውም የሚል አቁዋም የያዘ ሲሆን፣ የወልቃይት ህዝብ በትግራይ ክልል ስር ሆኖ የራሱ ልዩ ዞን ሊሰጠው ይችላል የሚል አቁዋም እያንሸራሸረ ነው፡፡ መሬት የሚባል ነገር መስጠት አይታሰብም የሚለው የክልሉ አቁዋም፣ ወልቃትን ወደ አማራ ክልል ለመጠቅለል የሚደረገውን ሙከራ በሃይል ጭምር እንደሚቀለብሰው ግልፅ አድርጉአል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤቱን ፣ የተወሰኑ የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለመጠቅለል የተጀመረውን እንቅስቃሴ የሚደግፉትና ከጀርባ ሆነው የህወሃትን ስራ ይሰራሉ የሚባሉት አቶ ያለው አባተ እንዲይዙት መደረጉ፣ ህወሃት በፌደራል መንግስቱ በኩል የሚሰጥ ውሳኔ በክልሉ ከሚሰጠው ውሳኔ ጋር እንዳይጋጭ ለማድረግ ሆን ብሎ የሰራው ስራ መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡ አቶ ያለው የብአዴን አባል ቢሆኑም፣ ለህወሃት ባላቸው ድጋፍ ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ ለፓርላማ የ6 ወራት የስራ እንቅስቃሴያቸውን ያቀረቡት አቶ ያለው፣ የማንነት ጥያቄ በቅድሚያ በክልሉ እንዲታይና ክልሉ የሚያቀርበውን መፍትሄ ስራ ላይ ማዋል ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የወልቃይት ጉዳይ ከአማራ ክልል ጋር ኩታ ገጠም እንደመሆኑና የድንበር ጉዳይ ያለው በመሆኑ ጉዳዩ በትግራይ ክልል ብቻ ሊታይ እንደማይገባ ጥያቄውን የሚያቀርቡ ወገኖች ይናገራሉ፡፡
ህወሃት መራሹ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የትግራይ ነዋሪዎች ወደ አካባቢው በመውሰድ ማስፈሩ፣ ችግሩ ገፍቶ ወደ ግጭት የሚያመራ ከሆነና ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ከታሰበ፣ ክልሉ የሚፈልገውን ድምጽ እንዲያገኝ ለማድረግ የታቀደ ሴራ ነው በሚል ይተቻል፡፡
No comments:
Post a Comment