ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)
እሁድ ምሽት በጅጅጋ ከተማ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የሟቾቹ ቁጥር በትንሹ 28 ደረሰ።
ለሊት ላይ በደረሰው በዚሁ የጎርፍ አደጋ የገቡት ያልታወቀ ከ50 በላይ ሰዎችን የማፈላለጉ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን የሶማሊ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን ሰኞ ምሽት በደረሰ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋም የሁለት ህጻናት ህይወት አልፏል።
በጅጅጋ ከተማ ዙሪያ ጥሎ የነበረውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 13 እንደነበር ቢገለፅም ቁጥሩ በትንሹ 28 መድረሱን አሶሼይትድ ፕሬስ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።
በዚሁ አደጋ ከ80 የሚበልጡ ነዋሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ግምቱ በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ንብረትም መውደሙ ታውቋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በእንቅልፍ ላይ እያሉ በደረሰው በዚሁ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 55 ሰዎች የገቡበት አለመታወቁንና የነፍስ አድን ሰራተኞች ፍለጋቸውን ቀጥለው እንደሚገኙም ተውቋል።
በተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ በአፋር ክልል መጋሌና ዳሎል ወረዳዎች በትንሹ አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከ270 በላይ ቤቶችና ከ2ሺ በላይ ፍየሎች በጎርፍ ተወስደዋል።
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ከባድ ዝናብ በደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንደሚቀጥልና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችም ለአደጋው ተጋላጭ እንደሚሆኑ ማክሰኞ ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከወራት በፊት በሃገሪቱ የአየር ጸባይ ለውጥን የተከተለ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ይችላል ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
እሁድ ምሽት በጅጅጋ ከተማ ደርሶ በነበረው የጎርፍ አደጋ አንድ አባት ስድስት ልጆቻቸውንና ሁለት የቤተሰብ አባሎቻቸውን በጎርፍ ካጡ በኋላ በደረሰባቸው ሃዘን ራሳቸውም ከሰዓታት ቆይታ በኋላ መሞታቸው ይታወቃል።
በዚሁ አደጋ ጉዳይ የደረሰባቸውን ነዋሪዎች ለመርዳትም ርብርብ እየተካሄደ መሆኑን አሶሼይትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment