ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2008)
በአማራ ክልል በሚገኘው የሰቆጣ ወረዳ የተከሰተው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ ተጨማሪ ነዋሪዎች ወደ ደብረብርሃን ከተማ በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።
በቅርቡ ወደ ከተማዋ ተሰደው የነበሩት ከ30 በላይ የወረዳው ነዋሪዎችም ወደ ቀያችሁ ካልተመለሳችሁ ተብለው እርዳታ እንዳያገኙ እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በወረዳው የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሃገሪቱ በ1977 ዓም ተከስቶ ከነበረው የባሰ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ረቡዕ ብቻ ከ10 ነዋሪዎች ከሰቆጣ ወደ ደብረ-ብርሃን ከተማ መግባታቸውንም ተናግረዋል።
በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ሰፍረው የሚገኙት እነዚሁ ነዋሪዎች በተለይ እናቶችና ህጻናት ክፉኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ከምግብ እጥረት የተነሳ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የገለጹት አንድ አባት ወርደው ወደቀያቸው ካልተመለሱ ድጋፍ እንዳይሰጣቸው ሲል የከፈተባቸውን ዘመቻ እጅጉን ኣንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
በወረዳው ያለው የድርቅ አደጋ እጅጉን እየተባባሰ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በቀያቸው ምንም ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ መሰደዳቸውን አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች የእርዳታ ተቋማት በሃገሪቱ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በተለይ በአማራ ክልል የከፋ መሆኑን ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።
በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎም መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች ከመንግስት ጋር በመተባበር በለጋሽ ሃገራት በመዘዋወር እርዳታን እያሰባሰቡ እንደሚገኝ ረቡዕ መዘገባችን ይታወሳል።
ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ 10.2 ሚሊዮን ሰዎች ከሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ 800 ሚልዮን ዶላር አካባቢ ብቻ መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።
No comments:
Post a Comment