Thursday, September 3, 2015

የኢትዮጵያ መንግስት በታችኛው ኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎች ላይ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ መፈጸሙን የሚያጋልጥ ሪፖርት ይፋ ሆነ።

ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለጋሽ አገራት በተለይም የእንግሊዝ መንግስት ሪፖርቱን ቢደብቀውም፣ የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት ሪፖርቱ ይፋ እንዲሆን ባዘዘው መሰረት ይፋ ሆኗል።

ሰርቫይቫል ኢን ተርናሽናል ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ጥናቱን ያከናወኑት -የኢትዮጵያ ዋነኛ እርዳታ ሰጪ የሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ዲ.ዔፍ አይ ዲ የተሰኘው የም እራባውያን ለጋሾች ቡድን ፣ የአሜሪካ የረድ ኤት ድርጅት የሆነው -ዩ ኤስ ኤይድ እና የአውሮፓ ህብረት በሁለት ቡድን የላኳቸው ልኡካን ናቸው።
ልኡካኑ ባለፈው ዓመት በደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ወደታችኛው ኦሞ ሸለቆ በማምራት በዚያ የሚኖሩ ጎሳዎች ለልማት በሚል ያለፍላጎታቸው ከቦታቸው እንዲፈናቀሉ ስለመገደድና አለመገደዳቸው ምርመራ አድርጓል።
የአካባቢ ተቆርቋሪ የሆነው ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል – በጥናቱ የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ መጠነ-ሰፊ የሰ ብ ዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ የተመለከተ መሆኑን በመጥቀስ ፤የእንግሊዝ መንግስት ይህን ሪፖርት ሊያፍን ሙከራ አድርጓል በማለት በ እንግሊዝ መንግስት ላይ ወቀሳ አሰምቷል።
የእንግሊዝ መንግስት ሪፖርቱ “ዐለማቀፍ ግንኙነትን ያበላሻል” በሚል “ በመረጃ ነጻነት ህግ”መሰረት ይፋ እንዳይደረግ ቢያፍነውም፤ ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ለአውሮፓ ህብረት ይግባኝ በማለቱ ህብረቱ ሪፖርቱን እንደለቀቀው በመግለጫው ተመልክቷል።
በሪፖርቱ የ ኢትዮጵያ መንግስት ለሚገነባ ስኳር ፋብሪካ ለሸንኮራ አገዳ ተክል በማለት በርካታ የኦሞ ተወላጆችን በግዳች አንዳንዴም በህይወታቸው በማስፈራራት ከይዞታቸው እንዲፈናቀሉ ከማድረጉም በላይ የጎሳው የቀድሞ የአሰፋፈር መልክና አካባቢው ሙሉ በሙሉ እንደተለወጠ ተመልክቷል።
የአንድ ጎሳ ተወካይ ለአጥኝዎቹ በሰጡት አስተያዬት “{ በሚቀጥለው ዓመት እናንተ እዚህ ከመምጣታችሁ በፊት፤ መንግስት መጥቶ ገድሎ ይጨርሰናል።” ማለታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ነዋሪዎቹ ለሸንኮራ ተክል ተብሎ መሬታቸውን መነጠቃቸው፤ አሰፋፈራቸውም-ህይወታቸውና ኑሯቸው የተመሰረተበትን እርሻውንና በኣጨዳ ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረውን የወንዙን ዳርቻ እንዳሳጣቸው በጥናቱ ተገልጿል። –
አጥኝዎቹ ነዋሪዎቹ እንዲሰፍሩበት ስለተደረገ አንድ ቦታ በሪፖርቱ ሲያብራሩ፦”በጉብኝታችን ወቅት ሰፋሪዎቹ በሀዘንና በጸጸት ውስጥ ነበሩ።በቦታው ንጽህናን ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ባለመኖራቸው ሰፋሪዎቹ በደም ተቅማጥ፣ በወባ ወረሽኝና ባልታወቀ ራስ ምታት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤ ሁኔታው እንደዚህ የከፋ ቢሆንም መንግስት በራሳቸው ፈቃድ መሄድ የፈለጉትን እንኳ ከቦታው እንዲወጡ እንዳልፈቀደላቸው ነግረውናል።” ይላል።

የሰፋሪዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ለጋሾች ከዓለማቀፍ ህግ ጋር በማመሳከር ያወጡት መመሪያ በአካባቢው ጨርሶ ተዘንግቷል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት በታችኛው ኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎች ላይ እየፈጸመ ያለውን መጠነ-ሰፊ የሰብ ዓዊ መብት ረገጣ እስኪያቆም ድረስ ዓለማቀፍ ለጋሾች ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡትን እርዳታ እንዲያቆሙ ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ ይህን መሰል ጥሪ ቀደም ካለ ጊዜ አንስቶ ቢያቀርብም በለጋሾቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመሆኑን የጠቀሰው ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል፤ የእንግሊዝ መንግስት በ2014-15 የበጀት ዓመት 360 ሚሊዮን ፓውንድ እርዳታ መስጠቱን አመልክቷል። የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ወኪል ኤልዛቤል ሀንተር ከለጋሾቹ አንዱ የሆነው ዲ ኤፍ አይ ዲ በታችኛው ኦሞ እየተፈጸመ ስላለው የሰብ ዓዊ መብት ጥሰት የቀረበለትን ሪፖርት ለመመርመር ብቻ ሁለት ዓመት እንደ ወሰደበት ጠቅሰዋል።
ከ እንግሊዝ ታክስ ከፋይ ህብረተሰብ በግብር የሚሰበሰበውን በመቶ ሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ፓውንድ በእርዳታ እየተቀበለ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽመውን መንግስት ድርጊት ለመሸፈን የ እንግሊዝ መንግስት ሆነ ብሎ ሪፖርቱ ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን ሙከራ ማድረጉንም ኤልዛቤል ነቅፈዋል።
ኤልዛቤል ሀንተር አክለውም፦በአንድ ነገድ ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት፣ ቤቱ በሚፈርስበት፣ከብቶቹ በሚዘረፉበትና የሜሬት ይዞታው በሚነጠቅበት ጊዜ የእንግሊዝ መንግስት ለፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲል እንዳላዬ ዓይኑን ጨፍኗል ብለዋል።
በታችኛው ኦሞ ሸለቆ አካባቢ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን፤ አብዛኞቹ በመሬት ይዞታ ነጠቃ፣ በግዳጅ ሰፈራና በመሰል ጭቆናዎች እየተሰቃዩ ይገኛሉ።
ነዋሪዎቹ በስፋት መሬታቸውንና ሀብቶቻቸውን ማጣታቸው፤ አካባቢውን ከፍ ወዳለ ሰብ አዊ ቀውስ እንደሚመራው አንድ ባለሙያ አስጠንቅቀአል።
አንድ የአጥኝ ቡድኑ አባል በበኩላቸው ለሸንኮራ አገዳ ተክልና ለሌሎች ሥራዎች ተብሉ ከ500 ሺህ በላይ ሰራተኞች ወደአካባቢው መሄዳቸው በተጨባጭ በአካባቢው ግጭት ይፈጠራል የሚለውን ስጋት ጨምሮታል ብለዋል።

No comments:

Post a Comment