መስከረም ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ፍሽስት ወረራ ወቅት ለተፈጸሙት ዘግናኝ ግፎች የጣሊያን መንግስትና ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁና የተዘረፉት ቅርሶችና ንብረቶች ለኢትዮጵያ እንዲመለሱ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ዓለምአቀፍ ሕብረት ለፍትሕ ጥያቄውን አቀረበ።
በጣሊያን ወረራ ወቅት የጣሊያን ወራሪዎች በዓለም ላይ የተከለከለውን ካለስተር ቦንብ ተጠቅመው ንፁሃን ኢትዮጵያዊያንን ጨፍጭፈዋል፣የታሪክ ድርሳናትን ዘርፈዋል፣ውሃን በመርዝ በመመረዝ ንፁሃን ዜጎችንና እንስሳትን ገለዋል ። በአዲስ አበባ ውስጥ በሶስት ቀናት ብቻ ከሰላሳ ሽህ በላይ ንፁሃን ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከሁለት መቶ በላይ አብያተክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊይውያን በመላ አገሪቱ በግፍ ተገድለዋል።
ይህንን ዘግናኝ ግፍ ፍሽስቶች ሲፈጽሙ ቫቲካን ድጋፍ ታደርግ እንደነበርም በመረጋገጡ የታሪክ ድርሳናትን ቫቲካን እንድትመልስና ለፈጸመችው በደልም ይቅርታን እንድትጠይቅ የተጠየቀ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግፉን ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ሊያወግዘው እንደሚገባም ተገልጿል።
የፍሽስት ጣሊያን የጦር አበጋዝ ለነበረው ግራዚያኒ የቆመው ጣሊያን ውስጥ የቆመለት ሃውልት እንዲፈርስም ተጠይቋል። ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ፊርማ በማሰባሰብ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሲል ዓለምአቀፍ ሕብረት ለፍትሕ ጥያቄውን አቅርቧል።
No comments:
Post a Comment