ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ የተካሄደው የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጉባዔ መልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነትን የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ውሳኔ አሳልፎአል መባሉ የአዲስአበባን ነዋሪዎችን በማነጋገር ላይ ይገኛል፡፡
የግንባሩ ከፍተኛ አመሮች ጭምር በከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሰራር በመዘፈቅ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን እንቅፋት በሆኑበት በዚሁ ወቅት ፣ እነዚሁ ወገኖች ቆዳቸውን ቀይረው የመልካም አስተዳደር ተቆርቋሪ ሆነው መቅረባቸው አስገራሚ መሆኑን አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለገ የአዲስአበባ ነዋሪ ለዘጋቢያችን አስተያየቱን ሰጥቶአል፡፡
ድርጅቱ ቀደም ሲል ከአናቱ መበስበሱን በመሪዎቹ አንደበት ይናገር ነበር ያለው ይህ አስተያየት ሰጪ፣ በአሁኑ ወቅት ከመበስበስም ደረጃ ማለፉን ተናግሮአል፡፡ በየትኛው አገልግሎት ሰጪ መ/ቤት ጉቦ እንደመብት የሚጠየቅበት ዓይን ያወጣ ጊዜ ላይ ደርሰናል የሚለው አስተያየት ሰጪ፣ የፍትሕ የበላይነት፣ ዴሞክራሲያዊ መብትና እኩል ተጠቃሚነት በወረቀትና በኢትዮጽያ ቴሌቪዥን ብቻ የሚገኙ ከሆኑ ቆይተዋል ሲል ያስረዳል።
ዛሬ ሕዝቡ ከመማረር አልፎ በቃኝ የሚልበት ደረጃ ቢደርስም ገዥዎቻችን ግን መቶ በመቶ ሕዝብ መርጦናል በሚል ድራማቸውን እየከወኑ መምጣቸው በየትኛው መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት ያላቸውን ጉጉት ከማሳየት በስተቀር ስለመሻሻል የሚሰጠው ምልክት የለም ሲል አስተያቱን አጠቃሏል፡፡
«ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ አሁን አሁን ስብሰባ ማሳመሪያ መዝሙሮች እየሆኑ መጥተዋል » ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ፣ በወሬ የሚቀየር ነገር ቢኖርማ ኖሮ ገና ድሮ ስንት ነገር በተስተካከለ ይላሉ። ኢህአዴግ በእርግጥም ቆራጥ እርምጃ የመውሰድ አቅም ካለው ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳተፉበትን ሌብነት በማጋለጥና እርምጃ በመውሰድ ሊያሳየን ይገባል፣ ከዚያ ውጪ ሲያወሩ ቢውሉ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም በማለት ያክላሉ።
በየምንሰራበት መ/ቤቶች አንድ ለአምስት በግዳጅ እንድንደራጅ፣ የልማት ሠራዊት፣ የሕዝብ ከንፍ በሚል በመሰባሰብ ፖለቲካቸውን እንድንጋት ከመወትወት በስተቀር የሲቪል ሰርቪሱ አገልግሎት አሰጣጥ ማሽቆልቆሉን የተናገረው አንድ የመንግስት መ/ቤት ባልደረባ ሲሆን፣ ቅጥር፣ዕድገትና ዝውውር ከፓርቲ አባልነትና ታማኝነት ጋር መያያዙ ሰፊውን ሰራተኛ ለስራ ያለውን ፍቅርና ተነሳሽነት መጉዳቱን አስረድቶአል፡፡
ሰፊው ሰራተኛ በወርሃዊ ገቢው የሰቆቃ ሕይወት እየመራ ሲሆን በአንጻሩ ጥቂት የመንግስት ስልጣን የያዙ ሹማምንት ከገቢያቸው በላይ የተደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ ማየት ለኢትዮጽያ ሕዝብ ትልቅ ወርደት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ስርዓት ጥገናዊ ለውጥ አድርጎ እንዲቀጥልም ሊፈቀድለት አይገባም፣ በቃህ ነው መባል ያለበት ሲል ተናግሯል።
No comments:
Post a Comment