መስከረም ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ መስተዳድር የኢህዴግ ድርጅት ጽ/ቤት ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ ዙሪያ በከተማው 10 ክ/ከተሞች በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህ/ብ ክፍሎችን በሚያወያይበት መድረክ ፣ ነዋሪዎች አወያይ ካድሬዎችን ያስደነገጡ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በጉለሌ ክ/ከተማ ስር የሚገኙ የ10 ወረዳዎችን የህብረተሰብ ክፍል በያዘው የወረዳ 9 አዳራሽ በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ስብሰባውን የተካፈሉ ዜጎች ለኢሳት ገልጸዋል።
በእለቱ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ግንቦት7ትን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቧል። ጠያቂዎች ” የእውነት ለለውጥ ከሆነ የምታስቡት ግንቦት 7 የሚባል ጠንካራ የምሁራን ስብስብ ያሉበት ድርጅት እንዳለ እየሰማን ነው፤ ይህን ድርጅት አሸባሪ እያላችሁ በድርጅቱ ሰበብ ወጣቱ እንዲታሰርና ምሁራን ከሃገር እንዲሰደድ ምክንያት ሆናችኋል፣ ዕቅዱ እንዲሳካ ከተፈለገ፣ለውጥ እንዲመጣም ከተፈለገ ዕርቀ ሠላም መምጣት አለበት አለዚያ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይመጣ ከሁኔታዎች መረዳት እየተቻለ ነው” የሚል ይገኝበታል።
እንዲሁም ” ድርጅታችን የምትሉት የውሸት ነው፤ ድርጅታችሁ ገምቷል፣ ድርጅታችሁ ሸቷል፣ በአሁኑ ወቅት የ17 ብር ሽንኩርት ለአንድ ጊዜ ወጥ አይበቃም፣ ኑሮው ተወዷል፣የኮንዶሚኒየም ቤት የምትሉትንም በኑሮ ውድነት መክፈል አቅቶን አቋርጠናል እናንተ ግን ልማት ልማት ትላላችሁ፤ ህዝብ ጠግቧል፣ኢኮኖሚ አድጓል ትላላችሁ፣ ለምን ዝቅ ብላችሁ ወደ ታች አታዩም! ፤ መንገድ ሰርታችኋል ትክክል ነው! ባቡር ተጀምሯል ትክክል ነው! ነገር ግን በዚህ ልማት ሰበብ በዲዛይንና በመንገዱ አቅጣጫ እቅድ ችግር ብዙ ዜጎች ቦታቸውንና ቤታቸውን አጥተው ተጎድተዋል፤ አዳዲስ የመንገድ አስፋልቶች በስህተት ዕቅድ ምክንያት ፈርሰዋል! ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ያለበት ህዝቡ ነው ትላላችሁ ችግሩ ግን ከላይ ነው! ድርጅታችሁ ምንድን ነው የሚሰራው?” የሚል ጥያቄ ለካድሬዎቹ ቀርቦላቸዋል።
” ልማቱን ማየት አልቻላችሁም፣ በዓለም ፈጣን እድገት እያመጣን ነው ትላላችሁ፡፡ ሃገራችን እንዲታድግ ከተፈለገ ነገሮችን በግልጽ መነጋገር አለብን! ቆሻሻ ዘይት ከውጪ ታስገባላችሁ በምትኩ የሃገራችንን ንጹህ ዘይት ወደ ውጪ ትልካላችሁ! ቆሻሻ ዘይቱን እንኳን በአግባቡ ማግኘት አልቻልንም! ” የሚሉ አስተያየቶች ሲቀርቡ፣ አንዳንድ ደጋፊ አስተያየት ሰጪዎች መልስ ለመስጠት ሲሞክሩ፣ በተቃውሞ ጭብጨባ ንግግራቸው ተቋርጧል።
“ለምን ችግሩን ለመሸፈን ትሞክራላችሁ? አልሠራችሁም! የወረዳ አመራር ተብለው የሚሾሙት ምንድን ነው ስራቸው?” የሚሉ ጠንካራ ጥያቄዎች መቅረባቸውንም ተሳታፊዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment