መስከረም ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የህወሃት ነባር ታጋይና በሁዋላም የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( አብዴፓን) መስርተው ክልሉን ላለፉት 24 ዓመታት ሲመሩት የቆዩት አቶ እስማኤል አሊ ሴሮ፣ ከስልጣን ተነስተው ወደ ፌደራል ሲዛወሩ እርሳቸውን ለመተካት በተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ፣ ህወሃት የደገፋቸው ቡድኖች አሸናፊዎች ሆነው መውጣታቸውን የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።
ቀድም ብለው ፓርቲውን እንዲመሩ የተመረጡት ወጣቱ አቶ ጣሃ አህመድ ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር ቢሆኑም፣ ክልሉን በፕሬዚዳንትነት መምራት አይችልም የሚል ተቃውሞ የህወሃት ደጋፊና ታማኞች በሆኑት በጸጥታ ዘርፍ ሃላፊው በአቶ ስዩም አወል፣ በአቶ ሙሃመድ አምበጣና በአቶ እስማኤል ተነስቶባቸዋል። ምንም እንኳ በኢህአዴግና በደጋፊ ፓርቲዎች አሰራር መሰረት የድርጅት ሊቀመንበር የክልል ፕሬዚዳንት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ይህ አሰራር ለአቶ ጣሃ አህመድ አልተፈቀደም።
አቶ ጠሃ ወጣት፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት የማስተርስ ዲግሪ ያላቸውና በተወሰነ ደረጃም ቢሆንም የህወሃትን የሞግዚት አስተዳደር የሚቃወሙና በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናትን ለፍርድ ለማቅርብ የሚተጉ መሆናቸው የአቶ እስማኤልን ቡድንና የህወሃት አመራሮችን አላስደሰተም የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ። አቶ ጠሃን በመደገፍ አቶ አህመድ ሱልጣን፣ አቶ አወል አርባና አቶ ሙሃመድ ኡስማን ከጎናቸው ቆመዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ሲያደርጉት የነበረው ውዝግብ ክልሉ ለ3 ወራት ያክል በሞግዚት አስተዳደር እንዲመራ የተደረገ ሲሆን፣ የፌደራል ባለስልጣናት ወደ አካባቢው በመሄድ የአቶ አሊ ሴሮና የህወሃት ታማኞች አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ አድርገዋል።
39 መቀመጫ ባለው የድርጅቱ ምክር ቤት አቶ ጠሃ መሃመድ 16 ድምጽ ሲያገኙ ፣ የእሳቸውን ሹመት የሚቃወሙት የአቶ አሊ ሴሮ ደጋፊዎች ደግሞ 20 ድምጽ አግኝተዋል። ሶስት ሰዎች በስብሰባው ባለመገኘት ድምጽ አልሰጡም። የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ የድርጅቱ ሊቀመንበር ስልጣኑን የሚያጣው በ2/3ኛ ድምጽ ነው የሚል ሲሆን፣ በዚህ ስሌት መሰረት አቶ ጠሃን ለማውረድ 26 የተቃውሞ ድምጽ ቢያስፈልግም፣ የህወሃት ባለስልጣናት ህጉን በመጣስ አቶ ጠሃ በ20 ድምጽ ከ4 ወራት ሹመት በሁዋላ ከስልጣን እንዲወርድ አድርገዋል። በእርሳቸው ምትክ አዲስ ሰው ለመሾም እንቅስቃሴ መጀመሩንና በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት አዲሱ ሰው እንደሚሾም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የድርጅቱን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም
No comments:
Post a Comment