Wednesday, January 7, 2015

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ክርክር አደረገ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጠበቃው በአቶ አምሐ መኮንን አማካይነት፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ ላይ ክርክሩን አደረገ፡፡ ክርክሩን የተከታተለው የተወሰነበትን የሦስት ዓመታት የእስራት ቅጣት እየፈጸመ ባለበት በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዝዋይ እስር ቤት ሆኖ በፕላዝማ ነው፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ቀርቦበት የነበረው ክስ፣ እሱ የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሠራ በጋዜጣው በቅጽ 5 ቁጥር 177፣ ቅጽ 04 ቁጥር 149፣ ቅጽ 04 ቁጥር 146፣ ቅጽ 5 ቁጥር 166 እና በቅጽ 5 ቁጥር 197 ዕትም ላይ፣ በራሱና በሌሎች ሰዎች አመንጭነት የተጻፉ ጽሑፎችን አትሞ አውጥቷል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ፣ ‹‹በመንግሥትና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ እንዲያምፅ ቀስቅሷል፤ መንግሥትን በሐሰት ወንጅሏል፤ ስሙንም አጥፍቷል፤ የሐሰት ወሬዎችን በመዘገብና ለሕዝቡ በማሰራጨት የሕዝብን አስተሳሰብ እንዲናወጥ አድርጓል፤›› በሚል በቀረቡበት ሦስት ክሶች ከአሳታሚው ማስተዋል የኅትመትና ማስታወቂያ ሥራ ድርጅት ጋር ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡ ተመስገን ሦስት ዓመት እስራትና ድርጅቱ 10,000 ብር ተቀጥተዋል፡፡


የሥር ፍርድ ቤት የወሰነባቸው ቅጣት አግባብ አለመሆኑና ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ፍርደኞቹ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ የቅሬታ ነጥቦቻቸውን አስረድተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ቀጥተኛ ምስክርና በሰነድ የተጠናከረ ማስረጃ ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበ ቢሆንም፣ የሥር ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል በሚል ያቀረባቸውን ከላይ የተጠቀሱትን ዕትሞች መሠረት በማድረግ ብቻ ቅጣት እንደወሰንበት አስረድቷል፡፡

አንድ ጽሑፍ እንደ አንባቢው ዝንባሌና አረዳድ አቅም ሊያሳጣ፣ ሊያስደስት ወይም ምንም የተለየ ስሜት ላይሰጥ ከሚችል በስተቀር አንድ የታወቀ መለኪያ (Standard) ሳይኖርና ጥቅም ላይ እንዲውል ሳይደረግ፣ የጽሑፍ አዘጋጅ ወይም አሳታሚ በሥር ፍርድ ቤት ወንጀል ናቸው ተብለው የተገመቱት ወንጀሎች የመሥራትን ሐሳብ ከጽሑፎቹ ባሻገር በሌላ ደጋፊ ማስረጃ (Corroborative Evidence) ሳይረጋገጥ ማረጋገጥ እንደማይቻል አስረድቷል፡፡

ከጽሑፎቹ ብቻ በመነሳት ወንጀል ተፈጽሟል ማለት በፍርድ ቤቱ የተሰየሙት ዳኛ ግላዊ ውሳኔ (Subjective Decision) ከሚሆን በስተቀር፣ ከፍርድ ቤቶቹ የሚጠበቀውን የውሳኔዎች ተጨባጭነት (Objectivity) ፈጽሞ ሊያረጋግጥ እንደማይችል የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በአንድ ጽሑፍ የተገለጸን ሐሳብ በማየት ብቻ ፍርድ ቤቶች የጽሑፍ አዘጋጅ ወይም አሳታሚ ወንጀል ፈጽሟል በሚል ቅጣት የሚወስኑ ከሆነ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተረጋገጠውንና መሠረታዊ የሆነውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አተገባበር አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት መሆኑን የጋዜጠኛው ጠበቃ አስረድተዋል፡፡ ዜጎች የሚገልጹት ሐሳብ መቼ ወንጀል ሆኖ ሊያስቀጣቸው እንደሚችልና መቼ ደግሞ የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ባለማወቅና ግራ በመጋባት፣ በመብታቸው እንዳይጠቀሙ በተዘዋዋሪ ገደብ የሚጥል መሆኑ እንደማይቀርም አስገንዝበዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ ሐሳብን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው በሕግ ብቻ እንደሆነ የሚገልጸውን ድንጋጌ በግልጽ እንደሚቃረን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡

ክሱ ሲቀርብ በእያንዳንዱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ ሥር የተገለጸውን ወንጀል ያስረዳል በሚል የቀረቡት ማስረጃዎችና ለክሱ የሆኑት አምስት ጽሑፎች ብቻ መሆናቸውን ጠበቃ አምሐ አስረድተው፣ በጋዜጠኛ ተመስገንና በሌሎች አመንጭነት የተጻፉትና በጋዜጣው የታተሙት ጽሑፎችን መመልከት ቢቻል፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለው የተደነገገውን የሚቃረኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይ በአንደኛው ክስ ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ ያቀረባቸው የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች፣ በራሳቸው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ጋር የሚጋጩና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት፣ በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤቱ ሊገድብ አይችልም ተብሎ ከተዘረዘሩት ልዩ ሁኔታዎች ውጪ በመብቱ ላይ ገደብ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥባቸው ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መላክ ሲገባው፣ የሥር ፍርድ ቤት በማለፍ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ አቶ አመሐ ሰፊና ዘርዘር ያለ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ የሚቃወም የይግባኝ ማመልከቻቸውን በክርክር ካሰሙ በኋላ፣ ደንበኛቸው በራሱና በሌሎች አመንጭነት ጽሑፍ በማተሙ ጥፋተኛ መባሉ አግባብ አይደለም እንዲባልላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ጥፋተኛ የተባሉት (ጋዜጠኛ ተመስገንና አሳታሚ ድርጅቱ) በጋዜጣ ላይ በጻፏቸውና እንዲታተሙ ባደረጓቸው ጽሑፍ ብቻ በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደ ከመሆኑ አንፃር ጋዜጠኛ ተመስገን ከእስር እንዲፈታና በድርጅቱ ላይ የተጣለው የገንዘብ መቀጮ እንዲነሳ እንዲታዘዝላቸው፣ እንዲሁም በክሶቹ የተጠቀሱት የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6)ን የሚቃረኑ በመሆናቸው፣ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥባቸውና የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ታግዶ ጥያቄያቸው ለጉባዔው እንዲላክላቸው ዳኝነት በመጠየቅ አቤቱታቸውን አብቅተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም ለማለት ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


No comments:

Post a Comment