የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እኔ ዳኛ ነኝ እያለ ቢለፍፍም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የምርጫ ቦርድ የወያኔ/ኢህአዴግ የመሃል ተጫዋች እንደሆነ ይገነዘባል። ይህ የዳኝነት ካባ ለብሶ የወያኔን የአጥቂ መስመር የሚመራ አካል በአሁኑ ሰዓት ዋነኛው ስራው የዳኝነት ካባውን ተጠቅሞ ጨዋታው ሲጀመር ለቡድኑ ወያኔ የሚያሰጉትን ጠንካራ ተቃዋሚዎች እና ፖለቲከኞች ሰበብ አስባብ እየፈለገ (Disqualify) እያለ ምርጫው ውስጥ እንዳይገቡ መከላከል ነው። በመኢሕአድ እና አንድነት ፓርቲ ላይ እያደረገ ያለውን ልብ ይበሉ።
የወያኔው ቋሚ ተሰላፊ ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ ምርጫ ውስጥ እንዳይገቡ ቢከለክል ምርጫ ተብዬው ጨዋታ ሊኖር አይችልም፣ ስለዚህ ወያኔን በምርጫው ወቅት የሚያጫውቱት ቡድኖች ስለሚያስፈልጉ አንዳንዶችን ያሳትፋል።
የምርጫው ቦርድ ጨዋታው በሚካሄድበት ወቅት ቡድኑ ወያኔ ሲጠቃ የዳኝነት ካባውን ደርቦ ከች ይልና ባሰማራቸው የምርጫ ድምጽ ቆጣሪዎች እና ታዛቢዎች (ሁሉም የወያኔ ካድሬዎች ናቸው) አማካኝነት ኮሮጆ ዘቅዝቆና ቀመሩን አስተካክሎ ቡድኑ ወያኔ 99.6% ድምጽ በማግኘት እንዳሸነፈ ያውጃል።
እንኳን ደህና መጡ ወደ ወያኔ 2007 የምርጫ ጨዋታ!
አንድነት ፓርቲ የምርጫ ቦርድ የሸረበበትን ሴራ ለመቃወም እሁድ ጥር 17 – 2007 ዓ.ም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎችን ጠርቷል። ለዚህም አባላቱ የሰልፉን ጥሪ ለህዝብ ለማድረስ ከወያኔ ደህንነቶች ጋር እየተናነቁ ቅስቀሳውን ተያይዘውታል። መንግስት ተብዬው የወሮ በላ ቡድን አንድነት ፓርቲ በድንገት የጠራውን ሰልፍ እንዲተው ወይንም ቀኑን እንዲቀይረው ማስፈራራትንና መለማመጥን እያቀያየረ ለማግባባት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
እስርና ወከባም ተጧጡፏል!
ነብዩ ሃይሉ እስርን በተመለከተ እንዲህ ብሏል “ቀደም ሲል በደህንነት ሃይሎች በቅስቀሳ ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር የዋሉትን የአንድነት ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት አቶ ያሬድ አለማሁ እና አቶ ሲሳይ ጌትነት ለመጠየቅ ባልደራስ አካባቢ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ያመሩት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ለገሰ ተፋረደኝ ለእስረኞቹ እራት ለመግዛት በእቅራቢያው ወደሚገኝ ምግብ ቤት በማምራት ላይ ሳሉ ሲቢል በለበሱ ደህንነቶች አማካይነት ከዛንቺስ አካባቢ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸው ታውቋል፡፡”
እሁድ ጥር 17 – 2007 ዓ.ም የተጠራው ህዝባዊ ተቃውሞ አይታጠፍም! (አንድነት ፓርቲ)
ይህ በዚህ እንዳለ አንድነት ፓርቲ እሁድ ጥር 17 – 2007 ዓ.ም የተጠራው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደማይታጠፍ አሁን ባወጣው መግለጫው አሳውቋል።
“የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አንድነት በምርጫው ለመወዳደር መወሰኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እና ኢህአዴግ እያደረጉት ያለውን ስውር ደባ እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቢቆይም መፍትሄ የሚሰጥ አካል ባለመገኘቱ ምክንያት ‹‹መብታችንን ለማስከበር አንለምንም›› በማለት በነገው እለት ማለትም ጥር 17/2007 ዓ.ም በ5 ከተሞች የጠራውን ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በመንግስትና በተለያዩ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አካላት ፓርቲው የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ቀን እንዲቀይርና ከመንግስት አካላት ጋር ድርድር እንዳያደርግ ጥረት ቢደረግም የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በዛሬው እለት ባደረገው ልዩ አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባ ሰልፉ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች እንደሚደረግና ለዚህም የሚያስፈልገውን ክፍያ ለመክፈል መዘጋጀታቸውን በማረጋገጥ ስብሰባውን አጠናቀዋል።
ጥሪ ለተቃዋሚ ፓርቲዎችና አባላት ከአንድነት ፓርቲ
“የሰልፍ ትብብር ጥሪ ለእውነተኛ ተቃዋሚዎች በሙሉ!
አንድነት እሁድ ጥር 17 በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የሚያካሄደው ሰላማዊ ስልፍ ላይ እውነተኛ ተቀዋሚዎች ሁሉ በፈለጉት መልኩ በሰልፉ ላይ ትሳተፉ ዘንድ ጥሪያችንን በአክብሮት እናስተላልፋለን። በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ታላቅ ሰላማዊ ስልፍ ላይ የሰማያዊ፣ የመኢአድ፣ የመድረክ እና የዘጠኙ ፓርቲዎች አመራሮች እንድትሳተፉ በዚህ አስቸጋሪና ታሪካዊ ወቅት ከጎናችን እንደምትሆኑ እምነታቸን ነው።”
No comments:
Post a Comment