Tuesday, January 6, 2015

ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ ዝዋይ የታሰሩ 16 የፖለቲካ እስረኞች ጠያቂና ምግብ እንዳይገባላቸው ተከለከሉ

• የሰማያዊ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ባልደረባ እንዳይጠይቁ ተከልክለዋልበነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተርጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ በዝዋይ የፌደራል ማረሚያ ቤት ታስረው የሚገኙ 16 የፖለቲካ እስረኞች ባልታወቀ ምክንያት ጠያቂና ምግብ እንዳይገባላቸው ተከለከሉ፡፡ዛሬ ታህሳስ 28/2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ም/ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ የገናን ዋዜማ ዝዋይ ከሚገኙ እስረኞቹ ጋር ለማሳለፍ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ዝዋይ አቅንተው የነበር ቢሆንም ሊጠይቋቸው ያስጠሯቸው የፖለቲካ እስረኞች ‹‹በማንኛውም አይነት ሰው መጠየቅ አይችሉም፡፡ ምግብም አይገባላቸውም፡፡›› ተብለው ሳይጠይቁ ለመመለስ ተገደዋል፡፡ጠያቂዎቹ ‹‹የመጠየቅ መብት አለን›› በሚል ወደ ውስጥ ለመግባት ግፊት በማድረጋቸው ፖሊሶች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ አበበ ቀስቶ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ፣ ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ጀኔራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ ጠያቂና ምግብ እንዳይገባላቸው የተከለከሉትን የ16 የፖለቲካ እስረኞችን ስም ዝርዝር አሳይተዋቸዋል፡፡የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ባልደረባ ለእስረኞቹ ምግብና ጠያቂ እንዳይገባ የተከለከለበትን ምክንያት ለማጣራት ቢሞክሩም ፖሊሶች ‹‹የሚጣራ ነገር ስላለ ነው፡፡ እሱ እየተጣራ ነው፡፡›› ከማለት ውጭ ምክንያቱን በግልጽ ሊነግሯቸው አልቻሉም፡፡ክልከላው እስከመቼ እንደሚቆይ በውል የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን ከአዲስ አበባ ተነስቶ የገናን በዓል ዋዜማ ከእስረኞቹ ጋር ለማሳለፍ ወደ ዝዋይ ካቀናው የሰማያዊ ፓርቲ ልዑክ በተጨማሪ የእስረኞቹ ቤተሰቦችም በክልከላው ምክንያት ሳይጠይቁና ምግብ ሳያስገቡ ተመልሰዋለል፡፡

No comments:

Post a Comment