ጥር ፲፩(አስራ አንድ ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) አስተባባሪ የሆነው ወጣት ዘመነ ምረተአብ ትናንት ጥር 10 ቀን 11:00 አካባቢ በማክሰኝት ከከተራ በዓል ላይ ባልታወቁ ሰዎች ተወስዷል። አፋኞቹ ዘመነ ምረተአብን ወዴት እንደወሰዱትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እስካሁን አልታወቀም።
ቀደም ሲል የታሰሩት የመኢአድ የቀድሞ ዋና ጸሃፊ አቶ ተስፋየ ታሪኩ፣ የድርጅቱ የደቡብ ጎንደር ዋና ጸሃፊ የሆነው አቶ ጥላሁን አድማሴ እና የምራብ ጎጃም ዋና አደራጅ የሆነው መቶ አለቃ ጌታቸው በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ እየተገረፉና እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ተመልክቷል።
<< የመኢአድን አመራሮችን በማሰር የኢትዮጲያን ትንሳኤ ማዳፈን አይቻልም፤ እንደውም እየደረሰብን ያለው ግፍ መኢአድ በበለጠ መልኩ ያጠናክረዋል>>-ብለዋል የድርጅቱ የአዲስ አበባ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አወቀ አባተ።
በተመሳሳይ በአንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ አምደኛና የፓርቲው አባል የሆነው እስማኤል ዳውድ እንድሪስ ትናንት ማለዳ ከሌሊቱ 12 ላይ በሁለት ሲቪል በለበሱና በሁለት ታጣቂዎች ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዷል።
እስማዔል በፖሊሶች ሊወሰድ ሲል ስልክ ደውሎለት እንደነበር የገለጸው ጓደኛውና የድርጅት አጋሩ አናንያ ሶሪ፤ በስፍራው ሲደርስ ወላጅ እናቱ እየተመለከቱ ፖሊሶች ሲወስዱት ማየቱን ተናግሯል።
እስማ ኤል ወደተወሰደበት ጃን ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ከሶስት ጓደኞቹ ጋር መሄዳቸውን የገለጸው አናንያ፤ ፖሊሶች እስማዔልን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስዱት መኪና ላይ ሲጭኑት ፎቶ በማንሳቱ እሱንም እንዳሰሩትና ቃሉን ከተቀበሉ በሁዋላ እንደለቀቁት ተናግሯል።
እስማዔል በአሁኑ ወቅት የ 7 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆበት በቀጨኔ ፖሊስ ጣቢያ ይገኛል።
ቀደም ሲል የተገንጣዩ ቡድን አባል የነበረው መሳይ ትኩ፤ ሁዋላ ላይ ወደ ራሱ በመመለስ የተገንጣዮቹን ሴራ በማጋለጡ፤ የቅድስት ማርያም ነዋሪ በሆነው እና ዳን ኤል ሙላት በተባለው አብሮ አደጉ መደብደቡን ያወሳው አናንያ፤ በፓርቲያቸው አባላት ላይ እየደረሰ ያለው በደል እየከፋ መምጣቱን ተናግሯል።
ላለፉት ሶስት ዓመታት በጋዜጠኝነት ሲሰራ የቆየው አናንያ ሶሪ፤ ለመብትና ለነጻነት በሚደረገው ትግል የድርሻውን ለማበርከት ከቀናት በፊት አንድነት ፓርቲን በይፋ እንደተቀላቀለ ማሳወቁ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትርሲት ውቤ የተባለች የጎንደር ከተማ ነዋሪ ወጣት በቅርቡ በፌደራሎች ታፍና መወሰን እና እስካሁ የት እንዳለች አለማመታወቁን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል።
የኢንተርኔት ካፌና የፎቶ ኮፒ ንግድ ቤት ባለቤት የሆነችው ወጣት ትርሲት በአፋኞች የተወሰደችው፤ የተቃዋሚዎችን ፅሁፎችና መፈክሮች ኮፒ እያደረግሽ ህገ መንግስቱን በሀይል ለመናድ አሲረሻል በሚል ምክንያት እንደሆነ በወቅቱ በሥራ ቦታዋ አካባቢ የነበሩ የአይን እማኞች ተናግረዋል። ቤተሰቦቿ በተደጋጋሚ ወደ ፖሊስ ጣብያ እየሄዱ ያለችበትን ለማወቅ ያደረጉት ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
በሌላ በኩል ወጣቶች በከተራ እና በጥምቀት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርት እንዳይለብሱ ፖሊስ ሲያስጠነቅቅ ቢቆይም፤ <<መንግስት በእምነታችን አያገባውም፤ልብሳችንንም ሊመርጥልን አይችልም>> ያሉ ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርቶችን ለብሰው ወጥተዋል።
በየሰንበት ት/ቤቱ ሰማያዊ ቲሸርት እንዳይለብሱ ጥብቅ ትእዛዝ የተላለፈ ቢሆንም፤ በርካታዎቹ የሰንበት ተማሪ ወጣቶች የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ከምንም ሳይቆጥሩት ከመቼውም ወቅት በላይ በሰማያዊ ቲሸርት አሸብርቀው ታይተዋል።
የዛሬው የጥምቀት በዓል እንዲህ ሰማያዊ ሆኖ ነው የተከበረው፡፡ አዘጋጆቹ የቲሸርቱን ቀለም እንዲቀይሩ በደህንነቶችና በፖሊስ ወከባና ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም ‹‹የምንለብሰውን ልብስ ቀለም አትመርጡልንም›› ብለው ሰማያዊውን ቲሸርት ለብሰውት ውለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment