ከብዙ ዓመታት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ የኢሳይያስ አፈወርቂና የድርጅቱ አቀንቃኝ ነበረ፤ ዛሬ ከሌሎች ብዙዎች ጋር በመቃብር ውስጥ ያለው የመጀመሪያው የሪፖርተር መጽሔት በሙሉ ውዳሴ ኢሳይያስ አፈወርቂ ነበር፤ የሞተው መለስ ዜናዊ እያለ የሪፖርተር መጽሔት ኢሳይያስን በመጀመሪያ እትሙ ሲያወድስ ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ ደፋሩ የወያኔ አባት ስብሐት ነጋ ለኤርትራ ያለውን ልዩ ፍቅር በሚያስገርም ሁኔታ ገልጾ ነበር፤ ለኤርትራ ቆመን እንዋጋለን አስከማለት ደርሶ ነበር፤ መለስ ዜናዊ በልዩ ጥበቡ መጀመሪያ ኤርትራን ባዕድ አደረገ፤ ቀጥሎም ጠላት አደረገ፤ ክፉ ጦርነት ተደረገ፤ በጦርነቱ ያሸነፈ የለም፤ በፍርድ ግን ኤርትራ አሸነፈች ተባለ፤ ፍርዱ ዋጋ-ቢስ ቦሆንም!
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም
ዛሬ ደግሜ ሪፖርተር ሌላ ስብከት ይዞ መጥቶአል፤ በመጀመሪያ ሪፖርተር ጋዜጣ ለኢትዮጵያዊነት ያለውን ወይም የሌለውን ስሜት ከየት አመጣው? ብዬ እንድጠይቅ እገደዳለሁ፤ አንዱ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝብሀል መንነት የለን፤›› ብሎ በአጽንኦት ጽፎ ነበር፤ ዛሬ በሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ ላይ ያነበብሁት ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት እንዳለ ነው! ለመግቢያ ያህል ይበቃኛል፡፡
ሪፖርተር በታኅሣሥ 22/2007 ርእሰ አንቀጹ የሚከተሉትን ሀሳቦች ሊያስጨብጠን ሞክሮአል፤
1. ‹‹አንዱ የሌላውን ድክመትና ጉድለት ከራሱ ጥንካሬ ጋር እያወዳደረ ከማየት ይልቅ የአገርና የሕዝብ ጠላት አድርጎ መፈረጅ ይቀለዋለ፤›› ይህ የሚፈጸመው ‹‹በገዢው ፓርቲና ዋነኛ በሚባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ነው፤›› ማንም ኢትዮጵያዊ ይህንን ርእሰ አንቀጽ በትክክልና በጥሞና ሳይታለልና ሳይሞኝ ማንበብ አለበት፤ እዚህ ላይ ሪፖርተር በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መሀከል ያለውን ግብግብ በሁለት እኩዮች መሀከል የሚደረግ አድርጎ ይዘግበዋል፤ ገዢው ፓርቲ የሚለው በደንብ የታጠቀ የፖሊስና የጦር ሠራዊት፣ በሎሌለንት የሠለጠኑ ዓቃቤ ሕጎችና ዳኞች፣ በመደብደብና በማሰቃየት የሠለጠኑ የጸጥታ ሰዎችና መርማሪዎች፣ በአይጥ፣ በቱሀንና በቁንጫ የተወረሩ እስር ቤቶች ያለውን ገዢ ፓርቲ ባዶአቸውን ከቆሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ጎን ለጎን አቁሞ ይናገራል፤ እግዚአብሔር ያያል፤ ታሪክም አንድ ቀን ይዘግባል፡፡
2፣ ‹‹ቅራኔአቸውን አርግበው ለመራጩ ሕዝብ ውሳኔ ተገዢ እስካላደረጉ ድረስ ስለምርጫም ሆነ ስለዴሞክራሲ መናገር አስቸጋሪ ነው፤›› ይህ አሁንም ለሁለቱም በእኩልነት የተነገረ ይመስላል፤ እግዚአብሔር ያያል፤ ታሪክም አንድ ቀን ይዘግባል፡፡
3. ‹‹በመካከላቸው ያለው ጠላትነት ተጠናክሮ በቀጠለ ቁጥር ለውጭ ጠላት ያጋልጣል፤ ለአገር ብሔራዊ ደኅንነትም አደጋ ነው ..›› አሁንም መልእክቱ ለማን ነው? ሪፖርተር ለሁለቱም የሚናገር ይመስላል፤ ትክክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ያያል፤ ታሪክም ይዘግባል፡፡
4. ‹‹ገዢው ፓርቲ አገርን የመምራት ትልቅ ኃላፊነት ተሸክሞ ከተቃዋሚዎች ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር ፍላጎት የለውም፤ … ከዚያ አልፎ ተርፎ የተቃዋሚ ፖሊቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ያደናቅፋል፤ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙትን የመደራጀት፣ የመቃወምና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች የሚጻረሩ ድርጊቶችን እየፈጸመ ለሥነ ምኅዳሩ መጥበብ የራሱን አሉታዊ ሚና ይጫወታል፤›› ገና አሁን እውነትን ፍርጥ አድርጎ የመናገር ወኔ መጣለት፤ ከመጀመሪያውኑ ይህንን አስተሳሰብ ይዞ ቢነሣና ቢቀጥል ወደእውነተኛነት ትንሽ ጠጋ ይል ነበር፤ ፖሊቲከኛው አሸባሪ፣ ጋዜጠኛው አሸባሪ እየተባለ በሚታሰርበት አገር ጠመንጃ ይዞ ደረቱ ላይ የቆመበትንና በድንጋይና በረጋጩ ጫማ መሀከል ለመተንፈስ የሚያቃትተውን ሰው እኩል መውቀስ ትክክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ያያል፤ ታሪክም ይዘግባል፡፡
5. ‹‹… ሻዕቢያ ጥቃት ሊፈጽም የሚችለው በዋናነት … የአገር ውስጥ ተቃውሞ ትግል አጋዥ በመምሰል ነው፤ … .›› እንደዚያ ብለው ነው ወያኔን እየነዱ አዲስ አበባ ያስገቡት! እግዚአብሔር ያያል፤ ታሪክ ይዘግባል፡፡
6. ‹‹የኢትዮጵያ መልማትና ማደግ ለህልውናዬ አደጋ ነው ብሎ የሚያስብ ማንኛውም የጎረቤት አገር የኢትዮጵያ ፖሊቲካ የውስጥ ትግል እንዳይበርድ የበኩሉን ሚና አይጫወትም ብሎ አለመጠርጠር የዋህነት ነው፤›› ሱዳን ነው? ጂቡቲ ነው? የመን ነው? ኬንያ ነው? ሁሉም ተቃዋሚ የሚባሉትን እያነቁ የሚያስረክቡ ናቸው!
7. ‹‹ለአገር ብሔራዊ ደኅንነተና ክብር ሲባል የፖሊቲካ ኃይሎች ከገቡበት የቅራኔና የጠላትነት ማጥ ውስጥ ሊወጡ ይገባል፤›› ምክሩ በጣም ጥሩ ሲሆን ለማን እንደተሰነዘረ ግን ግልጽ አይደለም፤ ስለዚህም ተቀባይ ባለቤት የለውም፤ አጉል መመጻደቅ ይባላል!
No comments:
Post a Comment