ፖሊሶች የደረጃ እድገት እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል
የአማራ ክልል መስተዳደር በግንቦት 2007 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ተከትሎ አመጽ ከተከሰተ ለመቆጣጠር ያስችላል ያለውን ስልጠና ለክልሉ ፖሊስ፣ ለማረሚያ ቤት ፖሊስ፣ ለሚሊሻና ለመከላከያ ሰራዊት አባላት እየሰጠ መሆኑን ሰልጣኞቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ስልጠናውም፤ ለፖሊሶች በዞን እንዲሁም ለሚሊሻና ለፀጥታ ጉዳይ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች እየተሰጠ መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በቀጣዩ ምርጫ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚፈራውን አመጽ መቆጣጠር እንደሆነ የገለጹት የፖሊስ ምንጮች በተለይ ፖሊስና ፀጥታ ጉዳይ ከ‹‹ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ›› ጋር በመተባበር የደፈጣ ውጊያን ለመከላከል ‹‹የደፈጣ ውጊያ ስምሪት›› በሚል አጭር ስልጣና እየወሰዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም አገር ውስጥ አመጽ ያነሳል ተብሎ ከሚፈራው ህዝብ በተጨማሪ መሳሪያ ያነሱ ተቃዋሚዎች በምርጫው ወቅት ጦርነት ይከፍታሉ የሚል ስጋት በመኖሩ ነው ሲሉ ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡ በደብረማርቆስ ውስጥ ስልጠናውን የሚወስዱት ሰልጣኞች ማታ ማታ የተኩስ ልምምድ እንደሚያደርጉ አንድ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ምርጫውን ተከትሎ ይከሰታል ከተባለው አመጽና ታጣቂ ቡድኖች ያደርሱታል ተብሎ ከሚፈራው ጥቃት በተጨማሪ የጥምቀት በዓል ላይ አመጽ እንዳይነሳ መከላከል፣ ከተነሳም መቆጠጠር የስልጠናው የአጭር ጊዜ ግብ ነው ተብሏል፡፡
በስልጠናው ወቅት በተለይ ፖሊሶች ‹‹ልዩ ኃይልና ፌደራል ፖሊስ በስራችን ጣልቃ ስለሚገቡ ነጻነት የለንም፣ ፖሊስ የህዝብ ነው እየተባለ ህዝብ ግን ይጠላናል፣ በህገ መንግስቱ መሰረት የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ ሲገባን እርምጃ እንድንወስድ ከበላይ አካል እንታዘዛለን፣ ከፖለቲካው ገለልተኛ አይደለንም›› የሚሉና ሌሎች ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችንም አንስተዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሶች በቂ ደመወዝና ዩኒፎርም አይቀርብልንም የሚል ቅሬታ እንዳቀረቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በስልጠናው ወቅትም በተለይ ፖሊሶች ጠንካራ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን መሰንዘራቸው ተከትሎ ሁሉም የክልሉ የፖሊስ አባላት አንድ የደረጃ እድገት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል ተብሏል፡፡ ጥር 12007 ዓ.ም የጀመረው የ‹‹ፀጥታ ኃይሎች›› ስልጠና ቅዳሜ ጥር 9/2007 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጥር 7/- ጥር 11/2007 ዓ.ም ለሚሊሻዎች አመራሮች ተጨማሪ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጾአል፡፡
በታህሳስ ወር የታቦት ማደሪያው ለባለሀብት መሰጠት የለበትም በሚል የባህርዳር ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮች አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማታቸው እንዲሁም በደብረማርቆስና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ስልጠና ላይ የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስልጠናውን በመቃወም ሰልፍ መውጣታቸው በ‹‹ፀጥታ ኃይሎች› ስልጠና ወቅት መወያያ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ሁለቱ ክስተቶች የአማራ ክልል አስተዳደር በዚህ አመት አመጽ ይነሳል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል፡፡
No comments:
Post a Comment