ጥር ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዢውን ፓርቲ በሃይል ለማንበርከክ በትግል ላይ የሚገኙ የአርበኞች ግንቦት7 ሴት አባላት ጥሪያቸውን ያቀረቡት የመስክ ጉብኝት ለማድረግ ለተንቀሳቀሱት የኢሳት ጋዜጠኞች ነው።
ሴት አርበኞቹ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው አፈናና የመብት ጥሰት በስልጣን ላይ ያለውን የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በሃይል ለማንበርከክ ነፍጥ እንዲያነሱ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።
ለሁለት ወራት ያክል ከኢህአዴግ ታጣቂ የሰራዊት አባላት ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ስታደርግ ቆይታ በመጨረሻ ምንም ችግር ሳያጋጥማት ሌሎች አርበኞችን ለመቀላቀል መቻሉዋን የገለጸችው አርበኛ ሃብታም ታደሰ፣ ወያኔ ደካማ መሆኑን በጫካ ህይወቴ ለማረጋገጥ ችያለሁ ብላለች።
አርበኛ ሃብታም ገዢውን ሃይል ለማንበርከክ በሚደረገው ትግል ሴቶች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርባለች
ሌላዋ አርበኛ ሰላማዊት ትኩ በበኩሏ ሴቶች የግድ በረሃ መውረድ እንደሌለባቸው ገልጻ፣ ለነጻነት ለሚደረገው ትግል ባሉበት ቦታ ሁሉ ሆነው ሊደግፉ፣ ሊታገሉ ይችላሉ ብላለች።
አርበኛ ሰናይት ወርቅነህም እንዲሁ በኢትዮጵያ ውስት የሚታየው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን ገልጻ በውጭና በአገር ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ትግሉን ተቀላቅለው ታሪክ የጣለባቸውን ሃላፊነት ይወጡ ስትል መልክት አስተላልፋለች።
የኢሳት የጋዜጠኞች ቡድን ተዘዋውሮ ለመታዘብ እንደቻለው በርካታ ሴቶች ገዢውን ሃይል በመሳሪያ ለማንበርከክ ወስነው እየታገሉ ነው። አርበኞች ግንባርና ግንቦት7 ውህደት ከፈጸሙ በሁዋላ ከሌሎች ሃይሎች ጋር ትብብር እና ጥምረት በመፍጠር ገዢውን ፓርቲ በሃይል ለማንበርከክ እንደሚሰሩ መግለጻቸው መዘገቡ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አርበኞች ማህበር በአርበኞች ግንባርና በግንቦት7 መካከል የተፈጸመውን ውህደት በመደገፍ መግለጫ አውጥቷል። ማህበሩ በመግለጫው ኢትዮጵያን ከገባችበት ውድቀት ነጻ ለማውጣት የተናጠል ትግል እንደማያዋጣ በመግለፅ ድርጅቶቹ ያደረጉት ውህደት አስደሳች ነው ብሎአል።
No comments:
Post a Comment