ኢትዮጵያን በግፍና በዝርፊያ የሚገዛው የህወሀት ጉጅሌ በመንግስትነትና በወንበዴነት መሀል ያለውን ልዩነት ከ፪፫ ዓመት ስልጣን ዘመን ብኋላ እንኳን ሊገለጥለት አልቻለም። ወይም እንዳመችነቱ ሁለቱን እያምታታ መቀጠሉን እንደብልህነት ቆጥሮታል። መንግስት መሆንንና ባለህገመንግስት መባልን ከመቆነጃጃ ኩልነት ባልተናነሰ በለጋሾቻቸው ባዕዳን ፊት ይጠቀሙበታል እንጂ ለኛ ለዜጎቹማ ወንበዴነታቸውን ሊደብቁን እንኳን አይጨነቁም።በቅርቡ ህወሀት የትግራይ ሪፐብሊክ ለማቋቋም የክህደት ተግባሩን የጀመረበትን ፵ኛ ዓመት በዓሉን ትግራይ ውስጥ በማክበር ላይ ሳለ የቀድሞው የህወሀት ታጋይ ያሁኑ የሀገሪቱ ጦር ሎች ኤታማዦር ሹም ተብዬው ሳሞራ የኑስ የህወሀት መንግስት ያገራችን ገበሬ ወፎችን ከማሽላው ለመከላከል እንደሚጠቀምበት መስፈራሪቾ የሚጠቀምበት ሕገ መንግስት ላይ የተጠቀሰውን የሀገሪቱን ሰራዊት የፖለቲካ ገለልተኝነት ድንጋጌና ሰራዊቱ
“ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ይሆናል” የሚለውን የይስሙላ ህግ ባደባባይ አውልቆ ጥሎ ተቃዋሚዎችን የሚወነጅል ሰፊ ንግግር ሲያደርግ ተደምጧል። ሳሞራ ይህን ንግግር በሚደረግበት ቦታ አፋቸውን ከፍተው ከሚያደምጡት ውስጥ የሀገሪቱን መንግስት እንዳሻቸው የሚዘውሩት የወያኔ ሹማምንት ነበሩ። በዚህ ንግግር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የባዕዳን መሳሪያ ሆነው የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እንደሚፈታተኑ ሀይሎች በመቁጠር ፍጹም ሀሰትና ጅምላ ፍረጃ ሲያደርግ “እረ ይህ ነገር በመደበኛ ስራህ የስራ ዝርዝር ውስጥ አለመኖር ብቻ ሳይሆን የተከለከለ ነው” ያለው አልነበረም። ይህን መርዝ ከተናገረና ተቃዋሚዎችም ላይ ዛቻውን ካሰማና ከወነጀለ በኋላ የህወሀት ልዩ አገልጋይነቱንም ካረጋገጠ በኋላ “ለማንኛውም እኔ ወታደር ስለሆንኩ አይመለከተኝም” ይምትል የፌዝ የግርጌ ማስታወሻ ብጤ በመናገር ህወሀት እያምታታ የሚጠቀምበትን ውንብድናና መንግስትነት አደባልቆ የሚያደርገውን ጉዞ ካላንዳች ሀፍረት አመልክቶናል። መሰረታዊ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለባቸው ሀገሮች የዚህ ዓይነት እነጋገር ባደባባይ አሰምቶ ለቀናት በያዙት ስልጣን ላይ መቀመጥ አይቻልም። ውንብድናና መንግስትነት ድንበር ባጣባት ኢትዮጵያ ይህ ህግ መተላለፍ ሳይሆን በገሀድ የምንኖረው የውርደት ህይወት ከሆነ አመታት ተቆጠሩ።ግንቦት ሰባት የፍትሕ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ሀገሪቱን በቅንነት ለማገልገል ሰራዊቱን የተቀላቀለው ተራው ወታደርና የበታች ሹማምንት ይህንን መልዕክት በቅጡ ሊያደምጡት ይገባል ብሎ ያምናል። በየትኛውም ዘርፍ ያለው ሰራዊት አለቆቹ የህወሀት ስንቅ ተሸካሚዎች እንጂ የውዲቱ ሀገራችን ዘበኞችና ሉዓላዊነት አስከባሪዎች አለመሆናቸውን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። ሰራዊቱን እያዘጋጁት ያሉትም በደል የበዛበት የገዛ ወገኑ መብቱን በሚጠይቅበትና ለመብቱ በሚታገልበት ስዓት አፈሙዝ ወገኑ ላይ እንዲያዞር እንጂ የሀገርና የህዝብ ከለላ እንዲሆን አይደለም። ለነዚህ የወያኔ የጦር አለቆች መታዘዝ ለሀገሪቱ ዘብ መቆም ሳይሆን የህወሀት ሎሌነት መሆኑንም በቅጡ መገንዘብ ያሻል። ብዙዎች የሰራዊቱ አባላት ከዚህ ቀደም እንዳደረጉትና ዛሬም እያደረጉ እንዳሉት በተገኘው አማራጭ ሁሉ ሰራዊቱ ይህዝቡን ወገኖች እንዲቀላቀል ጥሪያችንን እናቀርባለን። በየከተሞቹ በራሳቸው በቁባቶቻቸውና በዘመዶቻቸው ስም የጦፈ ንግድ ፣ ፎቅ ግንባታና ፈንጠዝያ ላይ ያሉት የወያኔ የጦር አለቆች የቆሙት የራሳቸውን የዝርፊያ ስርዓት አደረሳቸው ድረስ ለማቆየት እንጂ ለሀገር ዘብነት አይደለም።ሀገራችን የዜጎቿ ሁሉ መብት ተጠብቆ ስልጣኑ በህገመንግስት ተገድቦ የሚሰራ መንግስት ያስፈልጋታል ይገባታልም። በህግ አምላክ ተባብለው ህግ አክብረው መኖር ባህላቸው ላደረጉ ህዝቦች ህግና ውንብድናን አደባልቆ የሚገዛ መንግስት አይገባንም። ሰራዊቱም ለሀገር አገልግሎቱ የሚገባውን ክብር የሚያገኝበት ስርዓት እንጂ ነጋ ጠባ በወያኔ ግምገማ ከሚሸማቀቅበት በወገኖቹ ላይ እንደባዕድ እንዲተኩስ ከመታዘዝ የሚላቀቅበት ስርዓት ይገባዋል።ከሳሞራ የእብሪትና ማናለብኝነት ንግግር የምንማረው የህወሀት የጦር አዛዦች የሀገሪቱ ወታደሮች ሳይሆኑ ህዝብ የናቁ ጭፍን ራስ ወዳድ፣ ዘረኛና ሀገር ዘራፊ ማፊያዎች መሆናቸውን ብቻ ነው። ይህን ሀቅ በተለይ በቅርብ ሆናችሁ የምትታዘቡ በተራ ውትድርናና የበታች መኮንኖች ሆናችሁ ሀገሪቱን ለማገልገል የገባችሁ የሰራዊቱ አባላት የህዝብና የሀገር ወገንተኝነታች ሁን ማረጋገጫ ጊዜው ነገ ሳይሆን ዘሬ መሆኑን ላፍታም ልትዘነጉ አይገባም።
No comments:
Post a Comment