Saturday, July 19, 2014

ወይንሸት ሞላ ክፉኛ ተደብድባ ዝግ ችሎት ቀረበች!

በትላንትናው እለት አንዋር መስጊድ ህዝበ ሙስሊሙ ሲደበደብ ወይንሸት ሞላ በስፍራው ነበረች። አንድ ከዚህ በፊት የሚያውቃት የደህንነት አባል በቀጥታ ወደሷ መጥቶ ይደበድባት ጀመር። በወቅቱ በስፍራው የነበረው በፍቃዱ ጌታቸው ስለሁኔታው እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር።

በወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆነችው ወጣት ወይንሸት ሞላ አብራኝ ነበረች፡፡ አንዋር መስጊድ በወንዶች መግቢያ ፊት ለፊት ካለው ህንጻ ላይ ሆነን ሁነቱን ስንከታተል ከአሁን ቀደም የሚያውቃትና ከህንጻ ላይ ሆኖ ሲቀርጽ የነበር ደህንነት ብቻዋን ነጥሎ እየደበደበ ወሰዳት፡፡  ‹‹ለምን ተወስዳታለህ!›› ብዬ በጠየኩበት ወቅት ከእነዛ ከመንገድ ተለቃቅመው ለድብደባ የተሰማሩት ወጣቶች መካከል አንዱ ሽጉጥ አወጣብኝ፡፡ ለመሳሪያ ልምድ የሌለው በመሆኑ ካርታው እግሩ ስር ወደቀበት፡፡ ወይንሸትን ይዘውም ወደ ውጭ ከነፉ!



ዛሬ ፍርድ ቤት ይዘዋት ቀርበዋል። ሁኔታውን የተከታተለው ዮናታን ተስፋዬ የታዘበውን እንዲህ በማለት ነው ያቀረበው። “እጇቿ ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡ ጣቷ አብጧል፡፡ ፊቷ ገርጥቷል፡፡ የግራ እጇ በፋሻ ተጠቅልሎ አንገቷ ላይ እንደታሰረ በአንድ ፖሊስ እርዳታ ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ ገብታለች፡፡” ብሎ ነበር። ጥቂት ቆይቶ ባስተላለፈው መልእክት ደግሞ “ወይንሸት ጭንቅላቷን በቀኝ በኩል ተፈንክታለች፡፡ ተሰፍቶ ይታያል፤ ቀኝ እጇ መሰበሩ ተረጋግጧል፡፡ ሰውነቷ በጣም መጎዳቱ ያስታውቃል፡፡ ከፍርድ ቤት መልሰው አዲስ አበባ ፖሊስ ከሚሽን ወስደዋታል፡፡ ማንም እንዲያያት አልተፈቀደም የፍርድ ሂደቱንም ማንም መከታተል አልቻለም፡፡ ስንቅ ማቀበልም ተከልክሏል፡፡” በማለት ሁኔታውን አስረድቷል።

አሁን በደረሰን ዘገባ መሰረት በዝግ ችሎት የቀረበችው ወይንሸት ሞላ 14 ቀን ተጨማሪ ምርመራ ተጠይቆባት፤ 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባታል፡፡ የፍርድ ቤቱን ሂደት ማንም ሰው እንዲከታተል አልተፈቀደም የህግ ሰውም እንዳያናግራት ተከልክሏል፡፡  አሁን ከማዕከላዊ አጠገብ በሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ቤት ነች፡፡ የፖሊስ ጣቢያው ኃላፊዎች ማንም ሰው ሊያያት እንደማይችልና ስንቅም ሆነ ልብስ ላልተወሰነ ቀናት እንዳይመጣ በማለት መልሰውናል፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ ይህን ይመስላል። ትንሽ ቆይተው እሷንም አሸባሪ ብለው መክሰሳቸው የማይቀር ነው። ሌላ የሽብር ክስ ከመስማታችን በፊት፤ ትክክለኛውን ነገር ከወዲሁ እንዲረዱት፤ ወይንሸት ሞላ ወደ አንዋር መስጊድ ከመሄዷ በፊት አግኝቷት የነበረው ዮናታን ቀደም ብሎ የዘገበውን እናስነብብዎ። እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር።

ወይኒ ትናንት ጠዋት ላይ ቢሮ ቁጭ ብዬ ከላፕቶፕ ላይ እንደተደፋሁ መግባቷንም ሳላስተውል . . .

“እዚህ አፍንጫችን ስር ይህን የመሰለ ሰላማዊ ትግል ሲካሄድ ቢያንስ ሄደን አንታዘብም!? እዚህች መርካቶ አጠገብ ተቀምጠን ዘመን እየተጋራን – ታሪክ እየተጋራን . . .” ስትል ቀና ብዬ አየኋት።  . . . ምንም ማለት አልደፈርኩም. . . ለብዙ ጊዜ አንዋር መስጂድ እሄድ ነበር (በተለይ ባለፈው ዓመት)  የግልና የፖለቲካ ስራ ጊዜ አይሰጥም እንጂ አሁንም ብገኝ ምኞቴ ነው ፤ ሰው በጨካኞች ተከቦ ለመብቱ በፅናት ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ሲጮህ መመልከት በራሱ ትልቅ መነቃቃት እና ተስፋ ይሰጣል፡፡

ወይኒን ተረዳኋት ግን ሰጋሁ፡፡ ምክንያቱም ወይኒ ቀጥተኛ ሰው ነች . . . የሰው ጥቃት አትወድም . . . ሰው ሲበደል እያየች ዝም የሚል አፍ አልፈጠረባትም . . . ትናገራለች በጣም ተቆጥታ ትናገራለች . . . እንኳን በቆመጥ ሲደበደቡ እያየች በክፉ ሲታዩም ይተናነቃታል . . . ከእንባዋ እየተናነቀች ምራቋን ውጣ ትናገራለች . . . ወይኒ እንዲህ ነች . . . ምናልባትም ይህ ተቆርቆሪ ስብዕናዋ ይሆናል ሰማያዊ ፓርቲ ከትማ ያገናኘን፡፡ እናም ሰጋሁ፡፡

እንጃ ቀልቤ የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድሞ አሳወቀኝ መሰል . . .  “ምንም እኮ አዲስ ነገር አይፈጠርም I’ve been there, you know, it’s all the same every Friday” ከልቤ አልነበረም …
“መርካቶ ጉዳይ አለኝ በዛው ሙስሊም ወገኖቼን አየት አየት አድርጌ እመለሳለሁ” ከነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ሽፈራዉ ጋር እንደምትሄድ ነግራን ሄደች። ጌች ተደብድቦ ሲመለስ እሷ በዛው ቀረች . . . የፈራሁት ሆነ የህወሓት ካድሬዎች እንደሚጠሏት አውቃለሁ፤ ግን ፅናቷ ያፅናናኛል፡፡

ጎንደር አብረን ታስረን የማይረሳ ትዝታ ቀርፃብኝ ነበር . . . የሳዑዲ መንግስትን ተቃውመን አደባባይ ስንወጣ ሶስት ጨካኝ ፌደራሎች ብቻዋን ደብድበዋት ኢያስፔድ ታቅፎ ከወደቀችበት ነጥቆ አስጥሏት ሮጦ ከጨካኞች ሲያመልጥ እንኳን በደከመ ሰውነቷ ወደ ተቃውሞው ለመመለስ ፍላጎት ነበራት . . . ማርች 9 የሴቶች ሩጫ ጊዜ ከጣይቱ ልጆች ጋር ከፊት ሆና እየመራች የህወሓት ደህንነቶች አይን ውስጥ መግባቷ በምርመራ ወቅት ለረጅም ሰዓት ያቆዩአት ነበር . . .

የሆነ ሆኖ የወይንእሸት ሞላ ዛሬ በእጃቸው ድጋሚ ገብታለች . . . በመጥፎ ሁናቴም ተደብድባ ተጎድታለች፡፡ ደስተኛ እንደሆነች ግን ውስጤ ይነግረኛል . . . እሷ ነፃ ነች የውስጧን ጥያቄ መልሳ ሰላም አግኝታለች፡፡

በርካታ ሙስሊም ወገኖቻችንም ይህ ሰላምና እርካታ በመከራና በእስር ውስጥ ሆነው እንደሚሰማቸው አምናለሁ፡፡ ለእውነት በፍቅርና በይቅርታ የቆሙ አይወድቁም ነብዩም መሲሁም ያስተማሩን ይህን ነው!!! በርቱ!” በማለት ነበር የትላንቱን ውሎ የገለጸው። ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀ ነው፤ ወይንሸት ክፉኛ ተጎድታ ጉዳይዋ በዝግ ችሎት ታየ። መልሰውም ወሰዷት። እኛም መጨረሻዋን ሰላም ያድርገው፤ በማለት እንሰናበታለን።


No comments:

Post a Comment